አዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ ከመስከረም 1 ጀምሮ ይተገበራል - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
የታሪፍ ማስተካከያው በአንድ ጊዜ የሚጨመር ሳይሆን ለአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚተገበር መሆኑን በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል
በበጀት ዓመቱ ተቋሙ 42.5 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አገልግሎቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲሱን የታሪፍ ማሻሻያ ከመስከረም 1 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታወቋል።
የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጃነር ሽፈራው ተሊላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከ50 ኪሎ ዋት እስከ 200 ኪሎ ዋት ድረስ የሚጠቀሙ ደንበኞች ድጎማ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል፡፡
ተግባራዊ የሚደረገው የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ የመኖሪያ ቤት ፣ የንግድ ፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ እንዲሁም የመንገድ መብራትን ታሪፍ ያካተተ ነው፡፡
በተጨማሪም የአገልግሎት ክፍያ፣ የሃይል ፍጆታ ሂሳብ ክፍያ እና የከፍተኛ ሃይል ጭነትን እንደሚጨምር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል ።
ዋና ስራ አስፈጻሚው 50 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች የማሻሻያ ታሪፉን 75 በመቶ፣ ከ50 እስከ 100 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች 40 በመቶ እንዲሁም ከ100 እስከ 200 ኪሎ ዋት ደግሞ 4 በመቶ ድጎማ እንደሚደርግላቸው ነው ያስታወቁት፡፡
በዚህም መሰረት አንድ በወር 50 ኪሎ ዋት በሰዓት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሆነ ደንበኛ ቀድሞ በነበረው ታሪፍ በኪሎ ዋት በሰዓት በወር ውስጥ 24 ብር ይከፍል የነበረ ከሆነ በአዲሱ ታሪፍ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ደግሞ 28 ብር እንደሚከፍል ተጠቁሟል ።
በኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ የተደረገው የታሪፍ ማስተካከያ በአንድ ጊዜ የሚጨመር ሳይሆን ለአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚተገበር መሆኑን በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የታሪፍ ማስተካከያው ተግባራዊ መደረግ የነበረበት ከሁለት አመታት በፊት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሊዘገይ እንደቻለ፤ አሁን ካለው አለምአቀፋዊ ዋጋ አንጻር የዋጋ ጭማሪው ፍትሀዊ ማስተካከያ የተደረገበት ነው ሲሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
80 በመቶ ግብአቱን ከውጭ ሀገር በውጭ ምንዛሬ እንደሚስገባ የገለጸው አገልግሎቱ በአለም አቀፍ ገበያ በግብአቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ጭማሪ ለመቋቃም እንዲሁም የጥገና እና የማስፋፍያ ስራዎችን ለማስኬድ ጭማሪው እንደሚያስፈልግ ነው ያስታወቀው
በሌላ በኩል አገልግሎቱ በ2016 ዓ.ም ለ427 ሺህ አዳዲስ ደንበኞች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለጸ ሲሆን በበጀት ዓመቱ 42.5 ቢሊዬን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።