ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል ፍጆታ ታሪፍ ሊወጣ ነው
በኢትዮጵያ በተሽከርካሪዎች የሚደርሰው የአየር ብክለት አስጊ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ
የአየር ብክለትን ለመቀነስ በመጪዎች ዓመታት የኤሌክትሪካ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ ተወጥኗል
በኢትዮጵያ በተለይም በከተሞች ከሚደርሰው የአየር ብክለት ትራንስፖርት (ተሽከርካሪዎች) የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል።
ከሀገሪቱ ተሽከርካሪዎች 80 በመቶ ያህሉ በሚገኙባት አዲስ አበባ በተጠና ጥናት በከተማዋ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ብክለት በተሽከርካሪዎች የሚደርስ ነው።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከ2012 እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ 470 በሚሆኑ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ላይ ባደረገው ጥናት በኢንዱስትሪዎችና በደረቅ ቆሻሻ ከሚደርሰው ብክለት በበለጠ 60 በመቶው የአየር ብክለት በተሽከርካሪዎች ይደርሳል።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ልቀት ከባድ ችግር መሆኑን ተመራማሪዎች የሚገልጹ ሲሆን፤ በተለይም ለሰው ልጅ ጤና እና አካባቢ ጎጂ የሆኑ እንደ ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣ ካርቦን ሞኖክሳይድ፣ ሃይድሮካርቦን፣ ናይትሮጅን ኦክሳይድእና ቅንጣት ንጥረ-ነገሮች ልቀት ከፍተኛ ነው ይላሉ።
የልቀት መጠን ከፍተኛ ለመሆኑ የአብዛኛው ተሸከርካሪ እድሜ፣ የሚጠቀሙት የነዳጅ አይነትና የጭነት ክብደት ጉልህ ድርሻ እንዳለው የትራንስፖርት ባለሞያ ለአል ዐይን ተናግረዋል።
ይህም በመሆኑ የተሽከርካሪዎች የአየር ብክለት አስጊ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከተማ እና የአካባቢ ምህንድስና መምህር የሆኑት መሳይ ሸምሱ ገልጸዋል።
“አብዛኛው ከሰው እጅ ወደ ሰው እጅ የሚቀያየሩ ያረጁ መኪኖች ስለሆኑ ያሉት ነዳጅን ካለ ጎጂ ጭስ የማቃጠል ችሎታቸው በጣም አነስተኛ ነው። በአንድ ሊትር ነዳጅ ውስጥ በጣም ብዙ ጎጂ የሆነ ኬሚካል ወደ ከባቢ አየር ይለቃሉ። ሁለተኛ የምንጠቀመው የነዳጅ አይነት ካደጉት ሀገራት ከሚጠቀሙበት የነዳጅ የማጣራት ሂደት ደረጃው አነስተኛ ስለሆነ ነዳጁ በራሱ ብክለታማ ኬሚካሎችን አስቀድሞ ይዞ ነው ወደ እኛ የሚመጣው። ስለዚህ የሞተሮቻችን የማቃጠል ችግር በነዳጅ ጥራት ደረጃ ላይ የተደመረ ነው። ከዚህ በተጨማሪም እቃ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው የክብደት መጠን በላይ ስለሚጭኑ ሞተሮች ጎጂ ጭሶችን እንዳያወጡ የሚዳርግ ነው። ስለዚህ ለአካባቢ ብክለት የትራንስፖርት ዘርፉ ስጋት ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያገለገሉ ተሽከርካሪች ከመግባታቸው ባሻገር በአብዛኛው ከእጅ ወደ እጅ የሚቀያየሩ መሆናቸው እድሜያቸውን ከፍ አድርጎታል።የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚንስቴር በሀገሪቱ አማካኝ የተሽከርካሪዎች እድሜእስከ 25 ዓመት ነው ብሏል።
የትራንስፖርት ካርቦን ልቀቱ (ከአካባቢ አካባቢ ቢለያይም) ብዙ ሰዎች በሚኖሩባቸው ከተሞች እንደ ካንሰር ላሉ የጤና እክሎች እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ ድርቅና ጎርፍ ለመሰሉ አደጋዎች ተጋላነጭ እንደሚያደርግ መሳይ ሸምሱ ገልጸዋል። ብክለቱ እንዲቀንስ የማይሰራ ከሆነ ጉዳቱ እየከፋ እንደሚሄድም ባለሞያው ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ እንደ እንጦጦ ካሉ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ጠዋት የሚታው የጥቁር አየር ንጣፍ (ጉም) የከተማዋን የብክለት ሁኔታ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
መንግስት የትራንስፖርትን የአየር ብክለት ለመቀነስ ነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆኑና ያረጁ ተሽከርካሪዎችን መቀነስ እንደ አንድ መፍትሄ ወስዷል። የተሽከርካሪዎች የጭስ በዓመታዊ የተሽከርካሪዎች ምርመራ እንዲመረመር ደረጃ መውጣቱን ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚንስቴር ለአል ዐይን ተናግሯል። ይህም ከወጣው የጭስ ደረጃ በላይ ወደ ከባቢ የሚለቁ ተሽከርካሪዎች ማገድን ዓላማ ይዟል። የአጻጸም መመሪያው በቅርቡ እንደሚጸድቅም ተነግሯል።
መንግስት ከዚህ ባሻገርም ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍ ያለ ታክስ መጣልና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ደግሞ ማበረታቻ ማድረግ ብክለትን ለመቀነስ አቋም ይዟል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ አይኑን የጣለው መንግስት ሀገር ውስጥ እንዲገጣጠሙና ከቀረጥ ነጻ እዲገቡ ፈቅዷል።
ሚካኤል አስረሳኸኝ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከአራት ዓመታት በፊት ማሽከርከር ጀምረዋል። ይህም በኢትዮጵያ ከቀዳሚ የኤሌክትሪክ አሽከርካሪዎች ጎራ ያሰልፋቸዋል። በሞያቸው መካኒካል መሀንዲስ ሲሆኑ በግላቸው ተነሳሽነት ዘጠኝ የቤተሰቦቻቸውን የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ መቀየራቸውን ይናገራሉ። የነዳጅ ወጪን መቀነስ ቀዳሚውና ገፊው ምክንያት እንደነበር ቢገልጹም፤ ለሽግግሩ ቴክኖሎጂው ለካርበን ልቀት ያለውን በረከት እንደ እድል መውሰዳቸውን አንስተዋል። ከሁለት ዓመታት ወዲህም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ንግድ ላይ በመሰማራት ኮረንቲ ሞተርስ በተባለ ድርጅታቸው ተሽከርካሪዎችን ለገበያ እያቀረቡ ነው።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚንስቴር የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ ከድልማግስት ኢብራሂም ከከባቢ አየር ጋር የሚስማማ የትራንስፖርት ዘርፍ ለመፍጠር አቋም ስለመያዙ ተናግረዋል። መንግስት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነጻ እንዲሆኑ አድርጓል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች 15 በመቶ ብቻ የጉሙሩክ ታክስ እንደሚከፈልባቸው ያነሱት ስራ አስፈጻሚው፤ ይህም ለተሽከርካሪዎቹ መበራከት አበረታች ነው ይላሉ።
በዚህ የሚስማሙት ሚካኤል አስረሳኸኝ፤ የታክስ ማሻሻያው ወሳኝና አንድ እርምጃ ነው ይላሉ። ሆኖም ተሽከርካሪዎቹ እንዳይገቡ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ትልቅ መሰናክል መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ተሽከርካሪዎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዳይቀርቡ እክል ሆኗል።
“በዚህ አንድ ዓመት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከቤንዚንና ናፍጣ ተሽከርካሪዎች ይልቅ ዋጋ ቀንሰዋል። መኪኖቹ ከዚህ በታች ዋጋቸው እንዲቀንስ የሚያደርገው የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ነው። በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት እንደማንኛውም ሸቀጥ ዋጋቸው ከሚገባቸው በላይ ከፍ ያለ ነው” ብለዋል።
አነስ ያሉ የቤት መኪናዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ካለመቅረባቸው ባሻገር ገዥዎች ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ያላቸው እይታ እንደ አንድ ችግር ይታያል። በዋናነት ደግሞ ለተሽከርካሪዎች ኃይልን ጨምሮ የመሰረተ ልማት አቅርቦት በሚፈለገው ልክ አለመዘርጋት ተሽከርካሪዎቹ እንዳይስፋፉ ስጋት ያሳደረ ሲሆን፤ መንግስት ከባለሀብቶችና ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል። አሁን ላይ በመንግስትና ሌሎች አካላት የተሰሩ 40 የሚሆኑ የኃይል መሙያ (ቻርጅ ማድረጊያ) ማዕከላት እንደሚገኙ ከድልማግስት ኢብራሂም ጠቅሰዋል።
መንግስት የከባቢ ጥበቃ እርምጃውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በመግዛት ከፊት መምራት አለመቻሉም፤ ቁርጠኝነቱ አጠራጣሪ ስለማድረጉ የጠቆሞት ሚካኤል አስረሳኸኝ፤ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ የተገዙ 20 የህዝብ አውቶብሶችን ለአብነት አንስተዋል።
የብዙኸን ትራንስፖርት ከሚያደርሰው የብክለት ተጽዕኖ አንጻር ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም መሳይ ሸምሱ አሳስበዋል። ለዚህም የግል ባለሀብቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያሉ ሲሆን፤ መንግስት በሩን በመክፈትና በማበረታታት ለግል የብዙኸን ትራንስፖርት አቅራቢዎችና የኃይል ማዕከላት ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል።
የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ ከድልማግስት ኢብራሂም መንግስት ከ1300 በላይ የኤሌክትሪክ አውቶብሶችን ለመግዛት በሂደት ላይ ነው ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል ታሪፍ ለማውጣት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚንስቴር ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አሳውቋል። ሚንስቴሩ የህዝብ የኃይል መሙያ ማዕከላትን ቁጥር ለመጨመርም እየሰራሁ ነው ብሏል።
አሁን ላይ በሀገሪቱ ሰባት ሽህ የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ። በሚቀጥሉት ዓመታት ኢትዮጵያ 120 ሽህ የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች እንዲሁም አምስት ሽህ ገደማ አውቶብሶች ኢትዮጵያ ይኖሯታል ተብሎ ይጠበቃሉ።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኢትዮጵያ መጻኢ መሆናቸው እንደማይቀርም ተነግሯል። ከነዳጅ ወጪና ከብክለት አንጻር “ችግር በቅቤ ያስበላል” የሚሉት የኮረንቲ ሞተርስ ባለቤት ሚካኤል አስረሳኸኝ፤ ምርጫ ስለሌለን በሚል በሚቀጥሉት ዓመታት ተሽከርካሪዎቹ እንደሚስፋፉ ተስፈኛ ናቸው።