ውሀ እና ኤሌክትሪክ ላይ ፍጆታን መሰረት ያደረገ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማስከፈል ሊጀመር ነው
የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በውሃና ኤሌክትሪክ ላይ የሚጣለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚወስን መመሪያ በቅርብ ቀናት ውስጥ ይወጣል ብሏል
ከ8 ሰው በታች በሚጭኑ መኪናዎች የሚሰጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲጣል ተወስኗል
ውሀ እና ኤሌክትሪክ ላይ ፍጆታን መሰረት ያደረገ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማስከፈል ሊጀመር ነው።
የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በውሃ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል እና በትራንስፖርት አቅርቦት ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማስከፈል ሊጀመር መሆኑን ጠቁሟል።
የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅርቦት ላለፉት 22 ዓመታት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ተደርጎ የነበረው አነስተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ያለበትን የወጪ ጫና ለማቃለል በማሰብ እንደነበር መግለጫው አውስቷል።
“ከአንድ ቤተሰብ ወርሃዊ አማካይ ፍጆታ በላይ ኤሌክትሪክ እና ውሃን በብዛት የሚጠቀመው የመክፈል አቅም ያለው የህብረተሰብ ክፍል” ነው ያለው የገንዘብ ሚኒስቴር፥ አቅም ያለው የህብረተሰብ ክፍል ታክሱ የሚያስከትልበት የወጪ ጫና ስለሌለ ድጋፉ ትርጉም እንዳልነበረው ይጠቅሳል።
በአዲሱ የተጨማሪ እሴት አዋጅ አነስተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል በመኖሪያ ቤቱ የሚጠቀመውን አማካይ ወርሃዊ የውሃና ኤሌክትሪክ ፍጆታ ከታክሱ ነፃ ያደርጋል።
ከታክሱ ነፃ ከተደረገው በላይ የውሃና ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚጠቀሙ ዜጎች ላይ ግን የተጨማሪ እሴት ታክስ ተፈፃሚ ይሆናል ተብሏል።
በውሃና ኤሌክትሪክ ላይ የሚጣለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚወስን መመሪያ በቅርብ ቀናት ውስጥ እንደሚወጣና ተፈጻሚ እንደሚሆን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ከውሃና ኤሌክትሪክ ባሻገር ለ22 ዓመታት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ሆኖ የቆየው የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ አዋጁ ያስቀመጣቸውን ነጥቦችም ዘርዝሯል።
ከ8 ሰው በታች በሚጭኑ መኪናዎች የሚሰጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲጣል ተወስኗል ነው ያለው።
ባለሶስት እግር እና የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ግን ከተጨማሪ እሴት ታስ ነጻ እንዲሆኑ መደረጉን ነው የገንዘብ ሚኒስቴር ያስታወቀው።