የባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንዴት ይገመግሙታል?
የምጣኔ-ሀብት ባለሞያዎች ማሻሻያው በመንግስት ቁርጠኛነት ማነስ ግን ገቢራዊ መሆኑ አጠራጣሪ ነው ብለዋል
በእርምጃው የኢትዮጵያ ምጣኔ-ሀብት ወደ ጤናማ እስኪመለስ መንገራገጭ ይጠብቀዋል ተብሏል
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሀገሪቱን የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻሉን ይፋ አድርጓል።
እርምጃው የኢትዮጵያን ምጣኔ-ሀብትና ህዝብ ለረጅም ጊዜ “ከባድ” ችግር ውስጥ ከቷል የተባለውን የዋጋ ግሽበት እድገት ለመቀልበስ ያለመ መሆኑን ባንኩ አስታውቋል።
ብሄራዊ ባንክ “ስር የሰደደ ስጋት” ይሆናል ያለውን የዋጋ ግሽበት መንስኤና እርምጃዎችን ዘርዝሮ፤ መንስኤና እርምጃዎችን በማውጣት የገንዘብ ዝውውርንና የብድር እድገትን ለመግታት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
አምስት ውሳኔዎችን ያሳለፈው ባንኩ፤ ግሽበትን በ2016 ዓ.ም. ከ20 በመቶ በታች፤ በ2017 ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማድረግ ግብ በመያዝ ነው።
በ2016 ዓ.ም. የባንኮች የብድር ዕድገት በ14 በመቶ ጣሪያ እንዲገደብ፣ ብሄራዊ ባንክ ለመንግስት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድር በ25 በመቶ እንዲገደብ፣ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ለሚወስዱት አስቸኳይ ብድር ይከፍሉ የነበረው ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል፣ 30፤70 የነበረው የላኪዎች የውጭ ምንዛሪ ክፍፍል 50፤50 እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል።
አል ዐይን የፖሊሲ ማሻሻየው የታለመለትን ግብ ምን ያክል ይመታል፣ ገቢራዊነቱና የጎንዮሽ ጉዳቱን በተመለከተ የምጣኔ-ሀብት ባለሞያዎችን አነጋግሯል።
ባለሞያዎች እርምጃውን ለረጅም ጊዜ ሲወተወት የነበረ እንደሆነ ጠቅሰው “አዎንታዊ ለውጥ” እንደሚያመጣ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የምጣኔ-ሀብት ባለሙያ የሆኑት መቆያ ከበደ የማሻሻያውን ምንነት ተንትነው፤ እርምነጃው የተወጠነለትን ለውጥ እንዲሚያመጣ ተናግረዋል።
በተለይም በገንዘብ ህትመት ላይ የተመሰረተው የመንግስት የብሄራዊ ባንክ ብድርና የባንኮች የብድር እድገት መገደብ እንዲሁም ትዩዩ ገበያውን (ጥቁር ገበያ) ያናረው የላኪዎች የውጭ ምንዛሬ ክፍፍል ማሻሻያ መደረጉ ውጤት ያመጣል ባይ ናቸው።
በውሳኔው ብሄራዊ ባንክ ልል የሆነ ፖሊሲን መከተሉን አምኗል የሚሉት የምጣኔ-ሀብት መምህር የሆኑት ዶ/ር መዚድ ናስር በበኩላቸው፤ በተጨባጭ የተቀመጡ እርምጃዎች ከተተገበሩ “ትልቅ ተጽዕኖ ይመጣሉ” የሚል እምነት አላቸው። በተለይም መንግስት ለበጀት ጉድለቱ ከብሄራዊ ባንክ የሚበደረው ገንዘብ መገደቡ ጥሩ እርምጃ መሆኑን አንስተዋል።
አያሌ መንስኤዎች ላሉት የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው ብቻ ምን ያህል ፍቱን ሊሆን ይችላል ለሚለው የአል ዐይን ጥያቄ መቆያ ከበደ፤ ጉዳዩ ከቃሉ [የዋጋ ግሽበት ወይስ የዋጋ ንረት በሚል] ትርጓሜ ጀምሮ ምንጩም አከራካሪ ነው ይላሉ። ሆኖም በእሳቸው እምነት የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው ብቻውን ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ውሳኔ ነው።
በሀገሪቱ ወደ ገበያ የተለቀቀው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ የመጣ ግሽበት ነው የሚሉት የምጣኔ-ሀብት ባለሞያው፤ መፍትሄውም “ከገንዘብና ከገንዘብ አስተዳደር” ጋር የተያያዘ ነው የሚል እምነት አላቸው።
“ግሽበት ማለት የገንዘብ የመግዛት አቅም መቀነስ ማለት ነው። በአንድ ገበያ ወይም ምጣኔ-ሀብት ያለው የገንዘብ መጠን ሲጨምር የሁሉም እቃ ዋጋ ይጨምራል። ምክንያቱም ወደ ገበያ የሚገባው ገንዘብ እሴት የሌለው ገንዘብ ነው፤ ምጣኔ-ሀብቱ ከሚያመነጨው ሀብት በላይ የሆነ ገንዘብ ነው። እሴቱን ወይም የመግዛት አቅሙን የሚያገኘው ቀድም ብሎ ገበያ ላይ ካለው የመግዛት አቅምን እየተሻማ ነው። ስለዚህ እኔ [ችግሩ] ከገንዘብና ከገንዘብ አስተዳደር ጋር የተያያዘ ነው ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።
የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው ምንም እንኳ ለዋጋ ግሽበት መቀነስ አዎንታዊ ውጤት ቢኖረውም፤ የጎንዮሽ ጉዳቶች ግን አሉት።
ባለሞያዎቹ እርምጃው ንግድ፣ ኢንቨስትመንትንና የስራ እድል ላይ ጠበሳ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ሆኖም ከአንድ ችግር ለመወጣት መወሰድ ያለበት ስጋት ነው ባይ ናቸው።
“ባንኮች የሚያበድሩት መጠን ሲቀንስ ኢንቨስትምት በተወሰነ መልኩ ይጎዳል፤ ስራ ፈጠራም ይጎዳል። ዞሮ ወደ ምጣኔ-ሀብቱ ይመጣል፤ የማምረት መጠን ይቀንሳል። እኔ ባለፉት ሦስት አራት ዓመታት የሰራነው ስራ ማስተካከያ አካል አድርጌ ነው የማየው። የዋጋ ንረቱ ከሚያስከትለው ተጽዕኖ በላይ ምጣኔ-ሀብቱ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም” ሲሉ ዶ/ር መዚድ ተናግረዋል።
ሌላኛው የምጣኔ-ሀብት ባለሞያ መቆያ ከበደ እርምጃው ምጣኔ-ሀብት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ “ወደ ጤናማ እስኪመለስ መንገራገጭ ይኖራል” ብለዋል።
ብሄራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን በ2016 ዓ.ም. ከ20 በመቶ በታች እና በ2017 ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማድረግ ግብ ይዟል። ይህ አሀዛዊ ግብ ምን ያህል ይደረስበታል ለሚለው የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎቹ በእርምጃው “የታሰበውን ያህል ባይሆንም ግን ግሽበት ይቀንሳል” ብለዋል።
ባለሞያዎቹ የማሻሻያው ተፈጻሚነት ላይ ግን የመንግስት ቁርጠኝነት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። የመንግስት የበጀት ጉድለት ከፍተኛ መሆን እንዲሁም የውጭ የብድር ጫና፤ ግሽበትን ለመቀነስ የተደረገው ማሻሻያ ተግባራዊ የመሆን እድሉ አጣራጣዊ ነው ብለዋል።
የምጣኔ-ሀብት ባለሞያው መቆያ ከበደ “መንግስት በቀጥታ የሚወስደው ብድር ካላፈው ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ከ25 በመቶ በላይ አንሰጥም የሚለው የመፈጸም እድሉን አጠራጣሪ ያደርገዋል። ምክንያቱም ብሄራዊ ባንክ ገለልተኛ አይደለም። በቀጥታ በመንግስት ስር ነው ያለው። ሹሙም በቀጥታ በጠቅላይ ሚንስትሩ ነው የሚሾሙት። ስለዚህ አጠራጣሪ ነው። በተግባር የመፈጸም እድሉን አነስተኛ የሚያደርገው የበጀት ጉድለቱ ከፍተኛ መሆን ነው። ጉድለቱን በለሌላ መልኩ የመሙላት እድሉ አነስተኛ ስለሆነ ተግባራዊ የመሆን እድሉ አጠራጣሪ ነው” ብለዋል።
ዶ/ር መዚድ የዋጋ ግሽበት አስተሳሰብ ላይም የተመሰረተ በመሆኑ የውሳኔው ግማሽ ክፍል የማህበረሰቡን አስተሳሰብ መግራት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል የሚለው የእሳቸውም ጥያቄ መሆኑን አንስተዋል።
“በህብረተሰቡ ዘንድ መንግስት የዋጋ ንረትን ሊቆጣጠር ነው በማለት የዋጋ ንረት ሊጨምር አይችልም በማለት አስተሳሰብን ማስተዳደር ይቻላል። ምን ያህል ተጨባጭ ይሆናል የሚለው [ብሄራዊ ባንክ] ልል የሆነ ፖሊሲ እንድከተል አደረጉኝ ያላቸው ምክንያቶች አሁንም አሉ። ከውጫዊ ይልቅ ሀገራዊ ናቸው” ይላሉ።
መቆያ ከበደ በመንግስት በኩል ገቢራዊነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳለ ሁሉ እርምጃው ባንኮች ላይ አስገዳጅ በመሆኑ በከፊልም ቢሆን ሊፈጸም የሚችልበት እድል አለ ባይ ናቸው።