ኤሎን መስክ “የንግድና የመንግስት ተቋማት ትዊተርን ለመጠቀም ገንዘብ ሊከፍሉ ይችላሉ” አለ
አሜሪካዊው ቢሊየነር ኤሎን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊየን ዶላር ገዝቷል
መደበኛ ተጠቃሚዎች ግን ትዊተርን ያለምንመ ክፍያ በነፃ ይጠቀማሉ ብሏል
በቅርቡ ትዊተርን የገዛው አሜሪካዊው ቢሊየነር ኤሎን መስክ ትዊተር ከንግድና ከመንግስት ተቋማት መጠነኛ ክፍያ መቀበል ሊጀምር ይችላል አለ።
የቴስላ ኩባንያ ባለቤት እና ኃላፊ ኤሎን መስክ በቅርቡ ትዊተር የተሰኘውን የማህበራዊ ትስስር ገጽ በ44 ቢሊየን ዶላር መግዛቱ ይታወሳል።
ኤሎን መስክ በትዊተር ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ የመንግስት ተቋማት እና የንግድ ተቋማት ለትዊተር መጠነኛ ክፍያ ማስከፈል እንደሚጀምር አስታውቋል።
ሆኖም ግን “መደበኛ ተጠቃሚዎች ትዊተርን እንደ ሁል ጊዜ በነጻ መጠቀም ይችላሉ” ሲልም አስታውቋል።
አሜሪካዊው ቢሊየነር ኤሎን መስክ ትዊተርን መግዛቱን ተከትሎ በሰጠው አስተያየት፤ ትዊተር ላይ አዳዲስ አገልግሎቶችን በማካተት ገጹን አሁን ካለው የተሸለ እናደርጋለን ማለቱ ይታወሳል።
በተጨማሪም ገጹ ሰዎች በነጻነት ሃሳባቸውን የሚገልጹበት ገጽ ለማድረግ እንደሚሰራም ነው የተጠቀሰው።
አሜሪካዊው ቢሊየነር ኤሎን መስክ ባሳለፍነው ሳምንት የትዊተር ኩባንያን በ44 ቢሊየን ዶላር ለመግዛት ውል መፈጸሙ ይታወሳል።
እራሱን የነፃ ንግግር አራማጅ ብሎ የሚጠራው ማስክ የትዊተርን መዘመን ተችቷል። የፖለቲካ አክቲቪስቶች የማስክ አገዛዝ ማለት የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ የታገዱ ግለሰቦችን ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው መመለስ ማለት ነው ብለው ይጠብቃሉ።
አንዳንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የጥላቻ ንግግሮች እየጨመሩ ይሄዳሉ የሚል ፍራቻ ሲገልጹ፣ ወግ አጥባቂዎች ጥቂት ቁጥጥር ሊደረግ ይችላል ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።