ጃክ ዶርሴይ ከትዊተር ስራ አስፈጻሚነቱ ለቀቀ
አነጋጋሪ የኢትዮጵያ ጉዳዮች የሚንሸራሸሩበትን አምድ (ትሬንድስ) ለጊዜው የዘጋው ትዊተር በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ገደቦችን እንደጣለ ማስታወቁ ይታወሳል
ፕራግ አግራዋል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆኖ በኩባንያው ቦርድ በሙሉ ድምጽ ተሾሟል
ጃክ ዶርሴይ ከትዊተር ስራ አስፈጻሚነቱ መልቀቁን አስታወቀ፡፡
ከትዊተር የማህበረሰብ ትስስር ገጽ መስራቾች አንዱ የሆነውና ለ16 ዓመታት ያህል በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች ተቋሙን ማገልገሉን የገለጸው ዶርሴይ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ምክንያት ከዋና ስራ አስፈጻሚነቱ በራሱ ፈቃድ መልቀቁን ለተቋሙ ሰራተኞች በላከው የኢ-ሜይል መግለጫ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አሁንም “በአንክሮ” መከታተሉን እንደሚቀጥል ትዊተር አስታወቀ
የመጀመሪያው ተቋሙ ከመስራቾቹ ውጭ በሆኑ አካላት ይመራ የሚል ነው፡፡ በዚህም ስለ ታታሪነቱ የመሰከረለትና ከእያንዳንዷ የኩባንያው ወሳኝ ውሳኔዎች ጀርባ እንደነበር የተናገረለት ፕራግ አግራዋል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆኖ በኩባንያው ቦርድ በሙሉ ድምጽ መሾሙን እና በእሱ ሙሉ እምነት እንዳለው አስታውቋል፡፡
ሁለተኛው ምክንያቱ የቦርዱ ሰብሳቢ በነበረበት ወቅት በአባልነት የተቀላቀለውና ብሬት ቴይለር የተባለው መሃንዲስ የቦርዱ ሰብሳቢ ሆኖ በመሾሙ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ፌስቡክንና ትዊተርን በሀገራዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የመተካት እቅድ እንዳላት አስታወቀች
ብሬት ቦርዱን እየመራ ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግራል የሚል እምነት እንዳለውና በሹመቱ ደስተኛ መሆኑንም ገልጿል፡፡
ከፍ ያለ ተነሳሽነት እንዳላቸው የመሰከረላቸውን የተቋሙ ሰራተኞች በሶስተኛ ምክንያትነት አስቀምጧል፡፡ ከጀማሪ መሃንዲስነት ከፍ እስካሉ የኃላፊነት ደረጃዎች የደረሰውን ፕራግን ማሳያ አድርጎም አስቀምጧል፤ የሰራተኞቹን ተነሳሽነት ወደ ላቀ ውጤት የማሸጋገር አቅም እንዳለው በመጠቆም፡፡
ፕራግ ከዛሬ ጀምሮ በዋና ስራ አስፈጻሚነት እንደሚቀጥልና እሱም ከቦርዱ ጋር ሆኖ ሙሉ በሙሉ እስከሚለቅበት ጊዜ ድረስ ማገዙን እንደሚቀጥልም ዶርሴይ አስታውቋል፡፡
ከዚያ በኋላ ፕራግና ሌሎች አዳዲስ የተቋሙ አመራሮች ነጻነት ኖሯቸው እንዲሰሩና ተቋሙ ራሱን ችሎ እንዲቀጥል ለማስቻል ከቦርድ አመራርነቱ እንደሚርቅም ገልጿል፡፡ ውሳኔው ከራሱ የመጣ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡
ትዊተር ግልጽ ከሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል አንዱ እንዲሆን ያለውን ምኞትም ገልጿል ዶርሴይ፡፡
ዶርሴይ ከተቋሙ ውጤታማነት ጋር በተያያዘ ከስራ አስፈጻሚነቱ ሊወርድ እንደሚችል ሲነገር ነበር፡፡ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየመራ አይደለም ሲባልም ነበር፡፡
ትዊተር ከሚያራምዳቸው የተለያዩ አቋሞች እና ከሚጥላቸው ገደቦች ጋር በተያያዘ ብዙ ወቀሳዎች ሲሰነዘሩበትም ነበር፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ ተጠቃሚዎቹ ላይ የጣለው ገደብ ተጠቃሽ ነው፡፡
የጥላቻ ንግግሮችንና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ለመቆጣጠር በሚል ሽፋን የታዋቂ ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ የመንግስት ደጋፊዎችን ‘አካውንት’ በመዝጋት እንቅስቃሴያቸውን እየገደበ ነው የሚሉ ቅሬታዎች የሚሰነዘሩበት ትዊተር በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አሁንም “በአንክሮ” መከታተሉን እንደሚቀጥል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
አነጋጋሪ የኢትዮጵያ ጉዳዮች የሚንሸራሸሩበትን አምድ (ትሬንድስ) ለጊዜው መዝጋቱንና በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ገደቦችን መጣሉን ማስታወቁም አይዘነጋም፡፡