ትዊተር ተጠቃሚዎች ረጃጅም ጽሁፎቸን እንዲያጋሩ ለማስቻል እየሰራ ነው ተባለ
“ትዊተር አርቲክል” የተባለው አገልግሎቱ በቅርቡ ለተጠቃሚዎች ይፋ ሊደረግ እንደሚችል ታውቋል
ትዊተር ላይ ማጋራት የምንችለው ጽሁፍ በ280 ፊዳለት የተገደበ ነው
ትዊተር ተጠቃሚዎቹ በገጹ ላይ ረጃጅም ጽሁፎችን ማጋራት የሚችሉበት አገልግሎት ሊጀምር መሆኑ እየተነገረ ነው።
አዲሱ የትዊተር አገልግሎት “ትዊተር አርቲክል” የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን፤ ተጠቃሚዎቹ ያለ ምንም ገደብ ረጃጅም ጽሁፎችን ለተከታዮቻቸው ማጋራት የሚያስችል ነው ተብሏል።
የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጹ ላይ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ የሚያጋራው የጹሁፍ መጠን በ280 ፊዳለት የተገደበ መሆኑን ይታወቃል።
ትዊተር ይፋ ያደርጋል በተባለው አዲሱ “ትዊተር አርቲክል” የሚጋራው ጽሁፍ ላይ የፊደል ገደብ መኖር አለመኖሩ የተቃወቀ ነገር ባይኖርም፤ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሸለ መልኩ ረጃጅም ጽሁፎችን ግን ማጋራት ያስችላል ተብሏል።
የትዊተር ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ ሲኔት ለተባለ የቴክኖለጂ መረጃዎችን ለሚያስራጭ ድረ ገጽ በኢሜይል በሰጡት አስተያየት፤ “ትዊተር ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን ለተጠቃሚዎቹ ለማድረስ ይሰራል” ብለዋል።
“ትዊተር አርቲክል” ዙሪያም በቅርቡ ለተጠቃሚዎች አዳዲስ መረጃዎችን ይዘን እንቀርባለን ሲሉም አስታውቀዋል።
ትዊተር መጀመሪያ ላይ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ትዊት ማድረግ የሚችለው ፊደላት መጠን በ140 የተገደበ ነበር።
ኩባንያው በፈረንጆቹ 2017 የፊደላት ገደቡን ከ140 ወደ 280 ከፍ ማድረጉም ይታወሳል።