የትዊተር ባለቤት ኢሎን መስክ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ አስታወቁ
እንደፈረንጆቹ ህዳር 2021 ትዊተር ኩባኒያን የለቀቁት ጃክ ዶርሰይ ወደ ኃላፊነታቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ይገማታል
ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ኢሎን መስክ ከኃላፊነታቸው ይልቀቁ የሚል ድምጽ ሰጥተዋል
የትዊተር ባለቤት ኢሎን መስክ “የሚተካቸው አንድ ሞኝ ሰው" ሲያገኙ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ አስታወቁ፡፡
የቴስላ ዋና ስራ አስፈጻሚና አዲሱ የትዊተር ባለቤት ትዊተር ከገዙበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ትችቶች ሲያስተናግዱ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡
በተለይም ደግሞ የግል ጄት አውሮፕላናቸው የሚገኝበትን ቦታ በመግለጽ አንደኛው ልጃቸው ላይ ክትትል እና ትንኮሳ እንዲደርስበት አድርገዋል ያሏቸው ጋዜጠኞችን ጨምሮ የተለያዩ ሰዎች አካውንቶች ማገዳቸውና በኩባኒያው ውስጥ ለውጦች ማድረጋቸው በርካቶችን ያስቆጣ አጋጣሚ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዚህ የተማረሩት አሜሪካዊው ቢሊየነር ቀደም ሲል በከፈቱት ፕላትፎርም ከትዊተር ፕሬዝዳንትነት ይልቀቁ ወይስ አይልቀቁ በሚል የሚሰጠውን ድምጽ እንደሚከብሩ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
በተሰጠው ድምጽ መሰረት ከ10 ሚሊዮን (57.5 በመቶ) በላይ ሰዎች “አዎ” ከኃላፊነታቸው ይልቀቁ ብለው ድምጽ ሰጥተዋል።
ይህን ተከትሎም የትዊተር ባለቤቱ ኢሎን መስክ የሚተካቸው ሰው ሲያገኙ የትዊተር ዋና ስራ አስፈፃሚነቱን ለመልቀቅ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
መስክ ረቡዕ ረፋድ ላይ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ላይ "ስራውን የሚይዝ ሰው እንዳገኘሁ ከዋና ስራ አስፈጻሚነት ስራዬን እለቃለሁ! ከዚያ በኋላ የሶፍትዌር እና ሰረቨር ቡድኖችን ብቻ የማስተዳደር ይሆናል" ብለዋል፡፡ይሁን እንጅ ኩባኒያውን የመምራት አቅም ያለው ሰው ማግኘት ቀላል እንዳማይሆን መስክ ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ ሰዎች የተቋሙ መስራቾች ከሆኑት አንድ የሆኑትና እንደፈረንጆቹ ህዳር 2021 የለቀቁት ጃክ ዶርሰይ ወደ ኃላፊነታቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ግምታቸውን እያስቀመጡ ነው፡፡
በተጨማሪም በፌስቡክ ላይ ኃላፊነት የነበራቸው ሸሪል ሳንድበርግ፣ የመስክ የቅርብ ጓደኛ የሆኑት ኢንጂነር ስሪራም ክሪሽና እንዲሁም የዶናለድ ትርምፕ አማካሪና የልጅ ባል የነበረው ጃረድ ኩሽነር መስክን ይተካሉ ከሚባሉት በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡