የቴስላ እና ስፔስ ኤክስ ባለቤቱ ኤለን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊየን ዶላር ከገዛ በኋላ ትችት በርክቶበታል
የትዊተር ባለቤትና ቢሊየነሩ ኤለን መስክ ትዊተርን በስራ አስፈጻሚነት መምራቱን ለማቆም ወይንም ለመቀጠል ተከታዮቹ ሃሳባቸውን እንዲሰጡት ጥያቄ አቅርቧል።
መስክ “ከትዊተር መሪነቴ መነሳት አለብኝ ወይ? ለምትሰጡት ምላሽ ተገዥ ነኝ” የሚል ጽሁፍን በትዊተር ገጹ አጋርቷል።
ለ122 ሚሊየን የትዊተር ተከታዮቹ የቀረበው መጠይቅ የተለያየ ምላሽ እያገኘ ነው።
የትዊተር የቀድሞው ስራ አስፈጻሚ ጃክ ዶርሲ ጥያቂውን በጥያቄ መልሷል፤ “ለምን” ስለመልቀቅ አሰብክ የሚል መሰረታዊ ጥያቄን። መስክ ግን ለዶርሲ ምላሽ አልሰጠም።
የኤለክትሪክ ተሽከርካሪ አምራቹ ቴስላ እና ስፔስ ኤክስ ባለቤቱ ኤለን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊየን ዶላር ከገዛ በኋላ ያደረጋቸው ማሻሻያዎች እያሰተቸው ነው።
ቢሊየነሩ ትዊተርን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር አድርጎ ሰራተኛ ከመቀነስ ጀምሮ ያሻውን ውሳኔ እያሳለፈ መሆኑ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ተጠቃሚዎች ዘንድ ትዝብት ውስጥ እየጣላቸው መሆኑም ይነገራል።
በተለይ በቅርቡ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ለማስተዋወቅ የተከፍቱ የትዊተር አካውንቶችን እዘጋለሁ ማለታቸው ለድርጅቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ ስጋት እንዳይሆን ተሰግቷል።፡
ውሳኔው እንደ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ያሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ለትዊተር ምንም ሳይከፍሉ አዳዲስ ደንበኛና ገቢያቸውን ማሳደግ የለባቸውም ነው የሚሉት መስክ።
“በርግጥ ከትዊተር ውጭ ባሉት የማህበራዊ ትስስር ገጾች በርካታ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን እናውቃለን፤ ነገር ግን በትዊተር ማስታወቂያ እየሰሩ ደንበኞቻችን መቀራመት አይችሉም” ሲሉም በትቂተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የቀድሞው የትዊተር ስራ አስፈጻሚ ግን ይህ ምንም አይነት ነጥብ የሌለው ጉዳይ ነው በሚል አጣጥለውታል።
ትዊተር የማህበራዊ ትስስር ገጾች አድራሻዎቿን የለጠፈችውን የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ቴይለር ሎሬንዝ አካውንት ማገዱ ይታወሳል።
ውሳኔውን የሚተላለፉ አካላት የሎሬንዝ እጣ ይገጥማቸዋል ሲልም ኩባንያው አሳስቧል።
ይህም ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያስነሳ ኤለን መስክ አቋሙን ለዘብ አድርጎ ሆን ብለው ማስታወቂያ ከሚሰሩት ውጭ ማንኛውም የትዊተር ተጠቃሚ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ቢያጋሩ ግድ የለም ብሏል።
መስክ ትዊተርን ከገዛ በኋላ የድርጅቱን ግማሽ ሰራተኞች ቀንሷል።
ከሰሞኑ የጋዜጠኞችን አካውንት መዝጋቱም የመናገር ነጻነትን መገዳደ መጀመሩን ያሳያል በሚል የመንግስታቱ ድርጅትና የአውሮፓ ህብረት እየተቃወሙት ነው።
በዚህ ሁሉ ትችትና ተቃውሞ ውስጥ መስክ ስልጣን ልልቀቅ ወይስ ልቀጥል የሚል ጥያቄን ለተከታዮቹ አቅርቧል።