በትዊተር ተከታይ ብዛት ቀዳሚ 10 ሰዎችን "ወርልድ ኢንዴክስ" ይፋ አድርጓል
እንደ "ወርልድ ኢንዴክስ" ሪፖርት ከሆነ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የዓለማችን ብዙ የትዊተር ተከታይ ያላቸው ግለሰብ ተብለዋል።
የዘር ሀረጋቸው ከአፍሪካ የሚመዘዘው እና አሜሪካንን ለስምንት ተከታታይ ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት ባራክ ኦባማ 133 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተከታይ አላቸው።
ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር የገዙት የዓለማችን ሁለተኛው ሀብታም ኢለን መስክ ደግሞ በሁለተኝነት ተቀምጠዋል።
ከትዊተር በተጨማሪ የቴስላ እና ስፔስ ኤክስ ኩባንያዎች ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ኢለን መስክ 121 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተከታይ አላቸው።
ካናዳዊው ሙዚቀኛ ጀስቲን ቢበር ደግሞ 113 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተከታይ በመያዝ ሶስተኛው ብዙ የትዊተር ተከታይ ያለው ሰው ተብሏል።
ሌላኛዋ ሙዚቀኛ ኬቲ ፔሪ ደግሞ 108 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተከታይ በመያዝ አራተኛዋ ግለሰብ ሆናለች።
የዘር ሀረጓ ከካምቦዲያ የምትመዘዘው ሪሀና ደግሞ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ 107 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተከታዮች አሏት።
አሁን ላይ ክለብ አልባ የሆነው ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ106 ሚሊዮን ተከታዮች ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የፖፕ ሙዚቀኛዋ እና ተዋናይዋ ታይለር አሊሰን በ92 ሚሊዮን ፣የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ87 ነጥብ 8 ሚሊዮን፣ የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ በ85 ሚሊዮን፣ አወዛጋቢዋ ሙዚቀኛ ሌዲ ጋጋ በ84 ነጥብ 9 ሚሊዮን የትዊተር ተከታዮችን በመያዝ ከ7ኛ እስከ 10ኛ ድረስ ያለውን ደረጃ በቅደም ተከተላቸው መሰረት ይዘዋል።
በአፍሪካ ካሉት መሪዎች ውስጥ የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ በ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቀዳሚው ሲሆኑ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በአራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ተከታይ ናቸው።
የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት መሀመዱ ቡሀሪ በአራት ሚሊዮን፣ የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ በሁለት ነጥብ አምስት፣ የኡጋንዳው ዮሪ ካጉታ ሙሴቪኒ በሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን፣ የጋናው ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ በሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ተከታይ በማፍራት ቀዳሚዎቹ መሪዎች ናቸው።