የአለማችን ፈጣኑ ራፐር ኤሚነም በስሙ ያስመዘገባቸው ክብረወሰኖች ምንድን ናቸው?
“የራፕ ሙዚቃ ንጉስ” ነው የሚባልለት አሜሪካዊው ሙዚቀኛ በሰከንድ 7 ነጥብ 5 ቃላትን በማውጣት በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ሰፍሯል
ኤሚነም በስሙ ከ25 በላይ ክብረወሰኖችን አስመዝግቧል
ከ11 በላይ አልበሞችን (ከ340 በላይ ሙዚቃዎች) የሰራው አሜሪካዊው ራፐር ኤሚነም ሪከርዶችን መሰባበሩን ቀጥሏል።
የአለማችን ፈጣኑ ራፐር በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ውስጥ ስሙን በጉልህ ያሰፈረ ሙዚቀኛ ነው።
“የራፕ ሙዚቃ ንጉስ” እያሉ የሚጠሩት ኤሚነም ወይም በትክክለኛ ስሙ ማርሻል ማተርስ ከ25 በላይ ክብረወሰኖችን ሰብሮ ስሙን በድንቃድንቅ መዝገብ አስፍሯል።
በሚቺጋን ዴትሮይት ሙዚቃ የጀመረው የ51 አመቱ አሜሪካዊ ሙዚቀኛ የሂፓፕ እና ራፕ ሙዚቃን በማስተዋወቅ ረገድ ስማቸው ከሚጠቀስ አርቲስቶች መካከል ከፊት ይቀመጣል።
በፈረንጆቹ 1997 በሎስ አንጀለስ በተካሄደው የራፕ ኦሎምፒክ ያሳየው ድንቅ ብቃትና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሌላኛውን ተወዳጅ ራፐር ዶክተር ድሬ ትኩረት መሳቡ ይታወሳል፤ ይህ ውድድር ዶክተር ድሬ የኤሚነም ፕሮዲዩሰር እና ዋነኛ አማካሪ እንዲሆንም በር መክፈቱ አይዘነጋም።
ኤሚነም በ1996 “ኢንፋይናይት” የሚል መጠሪያ ያለው አልበም ቢለቅም በመላው አለም ተቀባይነት ያገኘው በ1999 የለቀቀው “ዘ ስሊም ሻዲ” አልበም ነው። ይህ አልበም ራፐሩ ሁለት የግራም አዋርድ እና አራት የኤምቲቪ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ሽልማትን እንዲያሸንፍ አድርጎታል።
ከዚህ አልበም በኋላ የለቀቃቸው የሙዚቃ ስራዎችም ኤሚነም በራፕ ሙዚቃ እንዲነግስ እና በርካታ ሽልማቶችን እንዲወስድ ያደረጉ አሁንም ድረስ ተወዳጅ የሆኑ ናቸው።
ኤሚነም “ጎድዚላ” የሚል መጠሪያ ባለው ሲንግል የሙዚቃ ስራው 225 ቃላትን በ30 ሰከንዶች (በሰከንድ 7 ነጥብ 5 ቃላትን) በማውጣት ክብረወሰን አስመዝግቧል።
6 ደቂቃ ከ4 ሰከንድ በሚረዝመው “ራፕ ጋድ” በተሰኘው ስራውም 1 ሺህ 560 ቃላትን ተጠቅሟል (በሰከንድ በአማካይ 4 ነጥብ 28 ቃላት)።
ኤሚነም በእያንዳንዱ የሙዚቃ ስራው አዳዲስ ቃላትን በመጠቀምም ክብረወሰን መያዝ ችሏል።
የአርቲስቶችን የተለየ የቃላት አጠቃቀም የሚያጠናው “ሚዩዚክ ስተዲ” እንደሚገልጸው ኤሚነም በ100 የሙዚቃ ግጥሞቹ ውስጥ 8 ሺህ 818 ቀደም ብሎ ያልተጠቀማቸውን አዳዲስ ቃላት ተጠቅሟል።
ራፐሩ በህይወቱ የገጠሙትን መሰናክሎች ብቻ ሳይሆን ሪከርዶችንም ደጋግሞ መሰባበሩን የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ በድረገጹ አስፍሯል።
በአሜሪካ የቢልቦርድ ሰንጠረዥ በምርጥ 200 አልበሞች ዝርዝር ውስጥ 6 ጊዜ በተከታታይ መግባት የቻለው ኤሚነም አልበሞቹ በአሜሪካ እና ብሪታንያ የተለያዩ ክብረወሰኖችን መስበር ችለዋል።
በአራተኛ የስቱዲዮ አልበሙ ውስጥ የተካተተው “ቲል አይ ኮላፕስ” ከሰኔ 2022 ጀምሮ በስፕቲፋይ ከ1 ነጥብ 36 ቢሊየን ጊዜ በላይ በመደመጥም ሪከርድ ይዟል።
ኤሚነም በ200 የለቀቀው 3ኛ የስቱዲዮ አልበሙ “ዘ ማርሻል ማተርስ ኤልፒ” በአሜሪካ በፍጥነት የተሸጠ የራፕ አልበም ነው፤ በአንድ ሳምንት ብቻ ከ1 ነጥብ 76 ሚሊየን በላይ ቅጂ ተሽጧል።
በአሜሪካ 61 ነጥብ 5 ሚሊየን አልበሞችን በመሸጥም በራፕ አልበሞች ታሪክ ትልቁ ሪከርድ ሆኖ ተመዝግቧል።
ኤሚነም ከ94 ሚሊየን በላይ የፌስቡክ ተከታዮችን በማፍራትም ከወንድ ሙዚቀኞች ቀዳሚው ሆኗል።
በመላው አለም ከ500 ሚሊየን በላይ የሙዚቃ አልበሞችን የሸጠው ኤሚነም በብሪታንያም በርካታ የሙዚቃ ክብረወሰኖችን ይዟል።
ዩቲዩብ ላይ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ተመልካች ያገኘው “ራፕ ጋድ” በቀጣይም ሪከርዶችን እንደሚሰብር ይጠበቃል።