"ኢትዮጵያን በኳሱም በአስተዳደሩም በካፍ ወደነበራት ሚና ለመመለስ እሰራለሁ"- ቶኪቻ አለማየሁ (ኢ/ር)
ኢ/ር ቶኪቻ "እግር ኳሱ መሸጥ አለበት" ብለዋል
የቀደሙ የተቋሙን አመራሮች በማሰባሰብ አማካሪ ምክር ቤት እንደሚያቋቁሙም ተናግረዋል
ቀጣዩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው የሚመረጡ ከሆነ ኢትዮጵያ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የእግር ኳስ ተቋማት ውክልና እንዲኖራት ለማድረግ እንደሚሰሩ ኢንጂነር ቶኪቻ አለማየሁ ተናገሩ።
ኢ/ር ቶኪቻ ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ከቀረቡ ሶስት እጩዎች መካከል አንዱ ናቸው። የግል ባለሃብቱ እጩነታቸውንና ቢመረጡ ሊሰሩ የሚችሏቸውን ተግባራት የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ/ም ሰጥተዋል።
በመግለጫው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እግር ኳስ መሰረት ከጣሉ ቀዳሚ ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗን ያነሱት ቶኪቻ አሁን ያለ ውክልና መቅረቷ ብዙ ነገር እንዳሳጣት ገልጸዋል።
"የካፍ መስራች ነን ዛሬ ግን በኳሱም በአስተዳደሩም የለንም፤ ስለዚህ ወደ ድሮ ሚናችን ለመመለስ መተጋገዝ በአመራሩም ውክልና እንዲኖረን ለማድረግ መስራት አለብን ብዬ አስባለሁ" ሲሉም ነው ያስቀመጡት።
እግር ኳሱ በቂ ገቢን ማመንጨት ባለመቻሉ "መንግስት ላይ ጥገኛ ሆኗል" ያሉም ሲሆን እዚሁ "ሃገር ውስጥ ጭምር መሸጥ" እንዳለበትም ነው ያነሱት።
ደጋፊዎች ወደ ሜዳ የሚገቡበትን፣ ሚዲያው በወጉ የሚዘግብበትን እና ጨዋታው ማህበረሰቡ ጋር የሚደርስበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል እቅድ ማዘጋጀታቸውንም ነው እጩው የተናገሩት፤ "እግርኳስ ራሱን የቻለ ኢኮኖሚ" መሆኑን በመጠቆም።
ለዚህ በግል ያላቸው ልምድ እንደሚጠቅማቸውም ገልፀዋል።
በእግር ኳሱ ውስጥ ባሉ "ሽኩቻዎቾ" ምክንያት አቅምና ተሰጥዖው ላላቸው ኢትዮጵያውያን የተዘጉ ብዙ የዘርፉ በሮች እንዳሉ በመግለፅም "የተዘጉትን በሮች ለመክፈት እሰራለሁ" ብለዋል ኢንጂነሩ።
'ትራዲሽናል' ያሉትን የፌዴሬሽኑን ተቋማዊ አሰራር በማስተካከል ተጠያቂነት ለሚኖርበት አሠራር መሠረት ለመጣል የሚያስችሉ ስራዎችን እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
የቀደሙ የተቋሙን አመራሮች በማሰባሰብና አማካሪ ምክር ቤት በማቋቋም ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርጉበትን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩም ነው የተናገሩት።
"በ2030ዎቹ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት ጭምር ማድረግ አለብን በሚል የ20 ዓመት ውጥን ይዘናል"ም ነው ያሉት ቶኪቻ።
"ከአሁን ቀደም በቀበሌ ጭምር ሳይቀር በየደረጃው ይካሄዱ የነበሩ ውድድሮችን ወደ ማህበረሰቡ መመለስ ያስፈልጋል"ም ብለዋል።
ቢመረጡ ከክልል ፌዴሬሽኖች ጋር የተሻለ ቅንጅትን በመፍጠር እግርኳሱን ለማልማትና ትክክለኛ የድምፅ ውክልና እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሚሰሩም ነው የገለፁት።
ፌዴሬሽኑ የጠቅላላ ጉባኤውን ቦታ በድንገት ከጎንደር ለመቀየር ስለመወሰኑ የሚሉት ነገር እንዳለ የተጠየቁት ባለሃብቱ "ስሜታዊነት የተሞላበት ውሳኔ ነው፤ ግለሰብ ነው ረብሻለሁ አለ የተባለው፤ እዚህም ላለመረበሹ ዋስትና የለም" ሲሉ መልሰዋል ውሳኔው ፌዴሬሽኑን በሚመሩ ግለሰብ መሰጠቱን በመግለፅ።
ፌዴሬሽኑን በድጋሚ በፕሬዝዳንትነት ለመምራት በእጩነት የቀረቡት የወቅቱ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ስለ ውሳኔው አግባብነት ተጠይቀው "እየደወለ በአካል ሄጄ ምርጫውን እበጠብጣለሁ የሚል አካል ባለበት ሁኔታ በተባለው ቦታ ልናካሂድ አንችልም" ሲሉ መመለሳቸውን አል ዐይን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ተገኝቶ መዘገቡ ይታወሳል።
ኢ/ር ቶኪቻ በስሩ በርካታ ተቋማትን የሚያስተዳድረው የኤልኔት ቢዝነስ ግሩፕ መስራች እና ባለቤት ናቸው። በቅርቡ ድሬዳዋ ላይ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ማስመረቃቸው የሚታወስ ነው።