በእግር ኳስ ጨዋታ መሃል ያለው እረፍት 25 ደቂቃ እንዲሆን ሃሳብ ቀረበ
ከ16 ዓመት በፊት የእግር ኳስ ጨዋታ እረፍት ከ15 ደቂቃ እንዳይበልጥ ስምምነት ተደርጎ ነበር
አዲሱ ሕግ በደቡብ አሜሪካ ሊተገበር እንደሚችል ይጠበቃል
የዓለም እግር ኳስ ማህበር ቦርድ በጨዋታ መሃል የሚኖረው የ15 ደቂቃ እረፍት ከፍ እንዲል ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።
ቦርዱ የእረፍት ደቂቃውን ከ15 እንዲበልጥ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላትና ጋር ውይይት ሊያደርግ መሆኑም ተገልጿል።
በእግር ኳስ ጨዋታ የመጀመሪው 45 ደቂቃ እንደተጠናቀቀ 15 ደቂቃ እረፍት ነበረ። አሁን ቦርዱ ያቀረበው ሃሳብ ግን ይህንን የ15 ደቂቃ እረፍት ወደ 25 ያሳድገዋል ተብሏል።
ወደፊት 25 ደቂቃ እረፍት እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን ይህም የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶች ለማድረግ ያግዛል ነው የተባለው።
በእግር ኳስ ጨዋታ መሃል ያለውን እረፍት 25 ደቂቃ የማድረግ ሃሳብ የመጣው ከአሜሪካው የሱፐር ቦል እንደሆነ ተገልጿል።
የመጀመሪያው ዙር 45 ደቂቃ ጨዋታ ከተደረገ በኋላ ጨዋታው ይቆምና ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል ገብተው ለ15 ደቂቃ እረፍት ያደርጋሉ። በፈረንጆቹ በ2006 በተደረገ የህግ ማሻሻያ ሥራ ላይ የ15 ደቂቃ እረፍት ከዚህ በላይ መጨመር እንደሌለበት ስምምነት ተደርሶ ነበር።
በአዲስ መልክ የቀረበውን ሃሳብ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ተግባር ላይ ሊያውለው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
የአውሮፓ ክለቦች እንደሚያደርጉት የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ሁሉ በደቡብ አሜሪካም የክለቦች ውድድር (ኮፓ ሊበርታዶርስ) አለ።
የዚህ ውድድር የዘንድሮ የፍጻሜ ተፋላሚዎች የብራዚሎቹ ፓልሜራስ እና ፍላሜንጎ ናቸው። በሁለቱ ክለቦች የፍጻሜ ውድድር ላይ በመሃል የሚኖረው እረፍት 25 ደቂቃ ሊሆን እንደሚችልና የመጀመሪያ ሙከራ እንደሚሆንም ነው የሚጠበቀው።
በእግር ኳስ 90 ደቂቃ ጨዋታ ከተደረገ በኋላ የግድ አንደኛው ቡድን ብቻ ማለፍ ካለበት 30 ደቂቃ ጭማሪ የተለመደ ነው። ይህ አሰራር ስራ ላይ የዋለው እ.አ.አ በ 1897 ነበር።
32 ቡድኖች የሚወዳደሩበት የአሜሪካ ብሔራዊ ሊግ የእግር ኳስ እረፍትን 12 ደቂቃ አድርጎ ነው የሚጠቀመው። እስከ አውሮፓውያኑ 1990 ድረስ የአሜሪካ ብሔራዊ ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ እረፍት 15 ደቂቃ የነበረ ሲሆን ከዛ ወዲህ ግን 12 ደቂቃ እንዲሆን ተወስኗል።የ 12 ደቂቃ እረፍት የሚደረገው ብዙ ጊዜ በብሐየራዊ ሊግ ጨዋታዎች ላይ ነው።