የሮማን አብራሞቪች ቼልሲ እግር ኳስ ክለብን የመሸጥ እቅድ ችግር ላይ ወድቋል ተባለ
የእንግሊዝ መንግስት አብራሞቪችን ጨምሮ በ7 ሩሲያዊ ቱጃሮች ላይ አዲስ የንብረት እገዳ መጣሉን አስታውቋል
እገዳው አብራሞቪች ቼልሲን ለመሸጥ በያዙት ውጥን ላይ ችግር መፍጠሩ ነው የተነገረው
የእንግሊዝ መንግስት መንግስት የቼልሲ እግር ኳስ ክለብ ባለቤት ሮማን አብራሞቪችን ጨምሮ በሰባት ሩሲያውያን ቱጃሮች ላይ አዲስ የሃብትና የጉዞ እገዳ መጣሉን አስታወቀ።
በቦሪስ ጆንሰን ጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመራው የእንግሊዝ መንግስት የክለቡ ባለቤት ከእንግሊዛውያን ባለሃብቶች ጋር ምንም ዐይነት ግብይቶችንም ሆነ የቢዝነስ ስምምነቶችን ማድረግ እንደማይችሉ አታውቋል።
ይህም ማለት አብራሞቪች እንዳሰቡት ሁሉ ቼልሲን ለመሸጥ አይችሉም ማለት ነው።
በአንድ ወቅት የአብራሞቪች የንግድ ሸሪክ የነበሩት ኦሌግ ዴሪፓስካ ተመሳሳይ እጣ ፋንታ ከገጠማቸው ቱጃሮች መካከል ናቸው።
የሩሲያ የነዳጅ ኩባንያ ሮዝኔፍት ኃላፊ ኢጎር ሼሺን ጨምሮ ሌሎች የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ሰዎች ናቸው የተባሉ አራት ሰዎች የእገዳው ሰለባ ናቸውም ተብሏል፡፡ እገዳው በቀጣዩ ሳምንት ተግባራዊ እንደሚደረግም ነው የተገለጸው።
ለፑቲን ደጋፊዎች የሚሆን ምቹ ሁኔታ እንደማይኖርም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን የተናገሩት። እገዳው ለዩክሬናውያን ያለንን ድጋፍ የሚያሳይ ነውም ብለዋል ጆንሰን።
በዩክሬናውያን ደም እጃቸው አለበት በሚል ቱጃሮቹን የከሰሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ በበኩላቸው አንገታቸውን ሊደፉ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በድምሩ 15 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገደማ የሚገመት የ7ቱ ቱጃሮች ሃብት ነው እገዳ የተጣለበት።