ከምህንድስና ስራው አንጻር ሲታይ የግድቡን ሙሌት ማስቆም እንደማይቻል የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ተናገሩ
ግድቡ ዘንድሮ 13.5 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር ውሃ ይይዛል ተብሏል
ተመራማሪው “ከምህንድስናው ሁኔታ አንጻር ሲታይ የግድቡን ሙሌት ማስቆም የሚቻልበት መንገድ” እንደሌለ ተናግረዋል
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የምህንድስና ስራ ሁኔታ የውሃ ሙሌትን ሊስቆም የማይችል ነው ሲሉ የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት መሀመድ በሺር መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከያዝነው ሳምንት መግቢያ ቀናት አንስቶ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መጀመሩ ይታወሳል።ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ስምምነት ላይ ሳይደረስ እንዳታከናውን ሲያሳስቡ የቆዩት ግብጽ እና ሱዳን በድርጊቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱን አገራት ጨምሮ የአረብ ሊግ የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ዙሪያ ጣልቃ አንዲገባ በጠየቁት መሰረት ዛሬ ሌሊት እንደሚመክር ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በህዳሴው ገድብ ዙሪያ የተከሰተው አለመግባባት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንጂ የጸጥታው ምክር ቤት ሊወያይበት አይገባም በሚል በአረብ ሊግ እና በሁለቱ ሀገራት የቀረበውን ቅሬታ ተቃውማ ለተመድ ደብዳቤ ጽፋለች።
በእንግሊዙ ማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ላለፉት 10 ዓመታት በህዳሴው ገድብ ዙሪያ ተመራማሪ የሆኑት መሀመድ በሺር ለቢቢሲ እንዳሉት ከምህንድስናና ከፊዚክስ አንጻር ሲታይ የግድብ ውሃ ሙሌት” ሊቆም የሚችልበት መንገድ የለም ብለዋል፡፡
“የግድቡ ግንባታ ዲዛይን ውሃ እየያዘ እንዲሄድ ተደርጎ የተቀረጸ በመሆኑ ግድቡ ውሃ እንዳይዝ ማድረግ አይቻልም” ብለዋል ተመራማሪው፡፡
በመጀመሪያ ዙር ሙሌት፣ከአንድ ዓመት በፊት 4. 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የያዘው ግድቡ በዚህ ክረምት ደግሞ 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚይዝ ይጠበቃል።ግድቡ በሁለት ማፋሰሻ ቱቦዎች በቀን ከ60 እስከ 100 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ወደታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንደሚፈስ ዘገባው ጠቁሟል።