የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለሱዳን ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው- አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ
የህዳሴ ግድበ ጉዳይን ፖለቲካዊና ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ የሚደረጉ አካሄዶች ቀባይነት የላቸውም
ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ መሙላት አታቆምም፤ 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌትም በተያዘለት መርሃ ግብር ይካሄዳል ብለዋል
የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለሱዳን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በሱዳን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ገለጹ።
አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በዛሬው እለት መቀመጫቸውን ሱዳን ካርቱም ላደረጉ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጠቀሜታን ይዞ የመጣ ግድበ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
አምባሳደር ይበልጣል በመግለጫቸው፤ “የህዳሴ ግድበ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሱዳን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው፤ ግድቡ በኢትዮጵያ ድንበረ ውስጥ ለሱዳን እየተገነባ ያለ ግድብ ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተጠናቀቀ ሱዳን በአነስተኛ ዋጋ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን እንድታገኝ የሚያስችላት መሆኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል።
እንዲሁም በሱዳን ውስጥ ያሉ የኤልክትሪክ ማመንጫ ግድቦች ዓመቱን በሙሉ በቂ ውሃ እንዲያገኙ እና ያለማቋረጥ ሀይል እንዲያመርቱ የሚያስችል ነው ሲሉም ተናግረዋል።
“ከህዳሴ ግድብ ግንብታ ጋር በተያያዝ ኢትዮጵያ ከሱዳን ምንም የደበቀችው ነገር የለም” ያሉት አምባሳደሩ፤ ወደፊትመ የምትደብቀው ነገር እንደማይኖራትም ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድበ ጉዳይን ፖለቲካዊ እና ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ የሚደረጉ አካሄዶችም ቀባይነት እንደሌላቸው አምባሳደሩ በመግለጫቸው አንስተዋል።
በአባይ ወንዝ ዙሪያ የሚደረግ የውሃ ክፍፍል ካለም ሁሉንም የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ያካተተ መሆን እንደሚገባውም በመግለጫቸው አክለዋል።
“ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንብታ እየገነባች ያለቸው እልክትሪክን ለማመንጨት ነው፤ ከዚህ ውጪ ሌላ አላማ የላትም” ያሉት አምባሳደር ይበልጣል፤ ሌሎችን መጉዳት ፍላጎት እንደሌላትመ አስታውቀዋል።
“ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌት አታቆምም” ያሉት አምባሳደሩ፤ ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትም በተያዘለት መርሃ ግብር እንደሚከሄድም ገልጸዋል።
ከ80 በመቶ በላይ ግንባታው የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በያዝነው የክረምት ወራት 18 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ እንደሚጀምር ይጠበቃል።
በነሀሴ 2013 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ሁለት ተርባይኖች 700 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት አንደሚጀምሩ የውሃ፤መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ከዚህ በፊት መናገራቸው ይታወሳል።
የፊታችን ነሀሴ ወር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫት እንደሚጀምሩ መገለጹ ይታወሳል።
ተርባይኖቹ እያንዳንዳቸው 350 ዋጋ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲሆን፤ በድምሩ በቅድመ ኃይል ማመንጨት ሥራው 700 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ ይሆናል።