ለህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ስኬት የመከላከያ ሰራዊት በአስተማማኝ ዝግጁነት ላይ ይገኛል- ሌ/ጄ አስራት ዴኔሮ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በያዝነው የክረምት ወራት 18 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ ይጀምራል
ሱዳንና ግብፅ ሙሌቱ ያለስምምነት እንዳይካሄድ ቢጠይቁም፤ ኢትዮጵያ ግን በተያዘው ጊዜ ለማከናወን ቁርጠኛ አቋም ይዛለች
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲከናወን በአካባበው የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት በአስተማማኝ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጅነራል አስራት ዴኔሮ ገለጹ።
ከ80 በመቶ በላይ ግንባታው የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በያዝነው የክረምት ወራት 18 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ እንደሚጀምር ይጠበቃል።
ሌተናል ጅነራል አስራት ዴኔሮ በቀጣናው ከሚገኙ የሠራዊት አባላት ጋር በታላቁ የህዳሴ ግድብ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ከመከላከያ ሚኒስቴር ፌስቡክ ገጽ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በውይይታቸውም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በትኩረት የሚከታተለውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በየደረጃው ባሉ አመራርና የሠራዊቱ አባላት ሌት ተቀን አስተማማኝ ጥበቃና ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ግንባታው ያለምንም እንቅፋት በታቀደለት መሠረት እየተፋጠነ እንደሚገኝም የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሌተናል ጅነራል አስራት ገልጸዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በማንኛውም ሰዓት በየትኛውም ቦታ ሰራዊቱ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ የተቃረበቸው ኢትዮጵያ፤ የውሃ ሙሌት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የግድቡን የግንበታ ሂደት መጎብኘታቸውን እና የግንብታው ሂደት በተያዘለት እቅድ እና ጊዜ መሰረት እየተከናወነ እንደሆነ መመልከታቸውን በዛሬው እለት አስታውቀዋል።
የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መቃረቡን ተከትሎ ሱዳን እና ግብጽ አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ ያላቸውን አቋም በማንጸባረቅ ላይ ይገኛሉ።
ሱዳን የጋራ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መካሄድ የለበትም ማለቷ የሚታወስ ሲሆን ፤ ግብፅም እንዲሁ በተደጋጋሚ ዛቻ አዘል መልዕክቶችን በተለያዩ ባለስልጣናቷ በኩል ስታስተላፍ ቆይታለች።
ሁለቱን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ የገለጸችው ኢትዮጵያ፤ የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትም በተያዘው ጊዜ እንደምታከናውን ቁርጠኛ አቋም ይዛለች።