ልኡኩ በትግራይ ክልል ካሉ አባቶች ጋር ሊያደርግ የነበረው ውይይት አልተሳከም አለ
በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የተመራው የሰላም ልዑኩ በመቀሌ ምንም አይነት መንፈሳዊ አቀባበልም ሆነ ሽኝት ሳይደረግለት ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል
ፓትሪያርኩና ብጹዕ አባቶች የኪዳን ጸሎትን በተዘጋ የቤተክርስቲያኒቱ ደጅ ላይ ለማድረግ መገደዳቸው ተገልጿል
ትናንት ማለዳ መቀሌ የገባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሰላም ልኡክ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል።
ልዑኩ መቀሌ ሲገባ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ አቀባበል እንደተደረገለት የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል በሚገኙ ብፁዓን አባቶች፣ ካህናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ምንም አይነት መንፈሳዊ አቀባበል አልተደረገለትም ተብሏል።
ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች የኪዳን ጸሎትን በተዘጋ የቤተክርስቲያኒቱ ደጅ ላይ ለማድረግ መገደዳቸውንም ነው የቤተክርስቲያኗ የቴሌቪዥን ጣቢያ የዘገበው።
የሰላም ልኡኩ በክልሉ የሚገኙ ብፁዓን አባቶችን በማግኘት ለማድረግ ያሰበው ውይይትም ሳይሳካ መቅረቱ ተገልጿል።
የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ እና የሰላም ልኡኩ አባላት በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቃሉ ወገኖች ጎብኝተዋል።
የሰላም ልዑኩ የመቀሌ ቆይታ ቅዱስ ሲኖዶስ የትግራይ ህዝብን በይፋ ይቅርታ ከጠየቀ ከቀናት በኋላ የተካሄደ ነው።
ብጹአን አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችን ያካተተው ልዑክ በቋሚ ሲኖዶስ እና በትግራይ አህጉረ ስብከት መካከል ተፈጥሮ የቆየውን ልዩነት ለማጥበብና ግንኙነቱን ለማደስ እንደሚያግዝ ቢታምነም የተጠበቀው አልሆነም።
የፌደራል መንግስቱ እና ሕወሃት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ግጭት ለማቆም ተስማምተው እርቀ ሰላም ወርዶ ግንኙነታቸውን ማደስ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስም ባለፈው ሳምንት ያለፈውን ምዕራፍ በይቅርታ እንዝጋው የሚል ጥሪ ማቅረቡና በይፋም የትግራይ ህዝብን ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል።
በትግራይ የሚገኙ ብጹአን አባቶች ግን ከአዲስ አበባ ለይቅርታ መቀሌ የገባውን ልኡክ ሊቀበሉት አልፈለጉም ተብሏል።