በሃይማኖታዊ ክዋኔና ባህላዊ ትውፊት የሚደምቀው የጥምቀት በዓል አከባበር በምስል
በዓሉ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ፣ ጎንደር፣ ጋምቤላ፣ ባቱና የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተከብሮ ውሏል
የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ዕለት በማሰብ የሚከበር በዓል ነው
የጥምቀት በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከብሯል።
በመላ ሀገሪቱ ትናንት ታቦታት ከአድባራት ወጥተው በካህናት፣ በዲያቆናት እና በምዕመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህሩ በመውረድ በዚያው ማደራቸው ይታወቃል።
ዛሬ ማለዳ በዓሉ ታቦታቱ ባደሩባቸው ጥምቀተ ባህር የተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ተከናውነው ስርዓት ጥምቀት ከተካሄደ በኋላም ወደየአጥቢያ ቤተክርስቲያናት ተሸኝተዋል።
በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የጥምቀት በዓል ሲከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት "የሰው ልጅ ዘላቂ ህይወትን መቀዳጀት የሚችለው መልካም ሰብዕና ሲላበስ እና ፈጣሪውን ሲፈራ ነው" ብለዋል።
ሁሉም ዜጋ ለሀገር ሰላም እና ዕድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመተሳሰብ እና በአብሮነት ለመቅረፍ መስራት እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።
ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ዕለት በማሰብ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ነው የተከበረው።
44 ታቦታት ከአድባራት የሚወጡባት ጎንደርም የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከብሮባታል።
በዓሉ በባህር ዳር፣ በሃዋሳ፣ በጅማ፣ በሻሸመኔ፣ በሆሳዕና፣ በባቱ፣ በደብረ ብርሃን፣ በነቀምቴ፣ በጋምቤላ ፣ በማይጨው ፣ ላሊበላና በተለያዩ አካባቢዎች ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቱንና ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ተከብሯል።