ህብረተሰቡ እርስ በእርስ በመዋደድ አንዱ ለፍቅር እንዲተጋ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ፡፡
የጥምቀት በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በመከበር ላይ ይገኛል።
በመላ ሀገሪቱ ትናንት ታቦታት ከአድባራት ወጥተው በካህናት፣ በዲያቆናት እና በምዕመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህሩ ሄደው ማደራቸው ይታወቃል።
ከዛሬ ማለዳም ጀምሮ የጥምቀት በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በመከበር ላይ ይገኛል።
የዓሉ አከባበር በጃንሜዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ የእምነቱ አባቶች እና መሪዎች እንዲሁም ምእመናን በተገኙበት በድምቀት ተከናውኗል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የጥምቀት በዓል ቤተክርስቲያኗ ፣ መንግስት እና ህዝበ ክርስቲያኑ ባደረጉት ጥረት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ወካይ ቅርስነት በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ዘርፍ በመመዝገቡ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ስርዓቱ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣም አደራ ብለዋል፡፡
በመልዕክታቸው እግዛብሔር ከእኛ የሚፈልገው እጅግ ቀላል፣ ዋጋ የማያስከፍል፣ ነገር ግን እጅግ ጠቃሚ ነው፤ እርሱም ፍቅር ነው ብለዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እርሱ እንደወደደን እኛም እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ይህን አዟል ፤ ይህ ትዕዛዝም የህሊና ቁርጠኝነት እንጂ ሌላ እያስከፍልም ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በጃን ሜዳ የጥምቀት በዓል ሲከበር ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ብቻ በተለይ የኦርቶዶክሳዊያን ሀብት የነበረው የጥምቀት በዓል ዘንድሮ የዓለም ሀብት በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የአለም ሀብት የሆነውን ይህን በዓል መላ ኢትዮጵያዊያን እንንከባከበዋልን ፤ እናሳድገዋለን ፤ ለአለም ህዝብም እናስተዋውቀዋለን ለዚህም ሃላፊነት እንወስዳለንም ነው ያሉት፡፡
ጥምቀት ዝቅ ማለትን ነው ያስተማረን ያሉት ምክትል ከንቲባው ሀገራችን እና ህዝባችንን ዝቅ ብለን በማገልገል ሀገር እና ህዝብ ከፍ እንዲሉ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡