የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ዋንጫዎችና ሜዳልያዎች በኤምሬትስና ኢትሃድ አዘጋጅቷል
የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በ38ኛው ሳምንት ሻምፒዮኑ የሚወሰንበት 10ኛው የፕሪሚየር ሊግ መርሃግብር ሆኗል
ሊቨርፑል ጀርመናዊውን አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ በክብር የሚሸኝበት ሁነትም ተጠባቂ ነው
የ2023/2024 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተመሳሳይ ስአት በሚደረጉ ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል።
ሻምፒዮኑን የሚወስኑት ሁለት ፍልሚያዎችም ይጠበቃሉ፤ ማንቸስተር ሲቲ ከዌስትሃም እና አርሰናል ከኤቨርተን።
የፔፕ ጋርዲዮላው ማንቸስተር ሲቲ ለአራተኛ ተከታታይ አመት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ዘጠነኛ ደረጃ የተቀመጠውን ዌስትሃም በኢትሃድ ይገጥማል።
ከሲቲ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብለው ሁለተኛ ደረጃን የያዙት መድፈኞቹ ከ20 አመት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት በኤምሬትስ ኤቨርተንን ማሸነፍና የሲቲን ነጥብ መጣል ይጠባበቃሉ።
ስፔናዊው የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ “እጣፋንታችን በእጃችን ነው ያለው፤ ሙሉ ትኩረታችን ዌስትሃምን ማሸነፍ ነው፤ ከዚህ ውጭ አዕምሮዬ ውስጥ የሚመላለስ ይህ ቢሆን ያ ባይሆን የሚል ሃሳብ የለም” ብለዋል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል መሪው ሚኬል አርቴታ በበኩሉ፥ “ፕሪሚየር ሊጉ በአለማችን ተወዳጁ ሊግ ነው፤ የእግርኳስ አፍቃሪዎችም በመጨረሻው ጨዋታ ምን ይፈጠራል የሚለውን በጉጉት እየጠበቁ ነው፤ በፍጥነት በሚለዋወጥ ትንቅንቅ ውስጥ የተሻለ ነገር ያደረገው ዋንጫውን ያነሳል” ብሏል።
የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በ38ኛው ሳምንት ሻምፒዮኑ የሚወሰንበት 10ኛው የፕሪሚየር ሊግ መርሃግብር ሆኗል።
ዋንጫውን የሚያነሳው ቡድን አለመለየቱን ተከትሎም ሁለት ተመሳሳይ ዋንጫዎችና ለሁለቱም ክለቦች ሜዳልያዎች ተዘጋጅተዋል ነው የተባለው።
ከኢትሃድ እስከ ኤምሬትስ ስታዲየም ያለው ርቀት 320 ኪሎሜትር ቢሆንም የውድድሩን ስሜት ከፍታ ለመጠበቅ ዋንጫውን እና ሜዳልያውን ወዲያውኑ ለሻምፒዮኑ ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል።
የፕሪሚየር ሊጉ አድናቂዎች ሙሉ ትኩረት በኢትሃድ እና ኤምሬትስ ስታዲየሞች ቢሆንም በአንፊልድ ለአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ የሚደረገው ሽኝትም ተጠባቂ ነው።
ከወልቭስ ጋር የሚያደርጉት የመጨረሻ ጨዋታ የጀርመናዊው አሰልጣኝ የ9 አመት ቆይታ ማጠናቀቂያ ይሆናል።
በፕሪሚየር ሊጉ አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን ያረጋገጠው አስቶንቪላ ከማንቸስተር ሲቲ፣ አርሰናል እና ሊቨርፑል ጋር የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ተቀላቅሏል።
ቶተንሃም፣ ቼልሲ፣ ኒውካስትል እና ማንቸስተር ዩናይትድ በዩሮፓ ሊግ እና ዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ የዛሬዎቹ ጨዋታዎች ወሳኝ ናቸው።