ኤቨርተን እና ዌስትሃም የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አሸናፊ ይወስናሉ
ማንቸስተር ሲቲ የሰሜን ለንደኑን ቶተንሃም በማሸነፍ ለአራተኛ ተከታታይ አመት የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ተቃርቧል
የ2023/24 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ በተመሳሳይ 12 ስአት ይደረጋሉ
ተጠባቂው የማንቸስተር ሲቲ እና ቶተንሃም ጨዋታ በሲቲ አሸናፊነት ተጠናቋል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በ51ኛው ደቂቃ ኧርሊንግ ሃላንድ ጎል እስኪያስቆጥር ድረስ የፔፕ ጋርዲዮላን ቡድን ነጥብ ሊያስጥለው እንደሚችል የሚያመላክት የጨዋታ እንቅስቃሴ አድርጓል።
አንጅ ፖስቴኮግሉ የተከተሉት ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት በሲቲ ላይ ጫናውን ቢያበረታም ሙከራዎቹ ወደ ግብ አልተቀየሩም።
ጉዳት የገጠመውን ብራዚላዊው ግብ ጠባቂ ኤደርሰን ተክቶ የገባው ስቴፈን ኦርቴጋም የቶተንሃምን ወደ ጨዋታው የመመለስ እንቅስቃሴ ገቷል።
ጀርመናዊው ግብ ጠባቂ የሰን ሁንግ ሚን ለጎል የቀረበ ሙከራ ያዳነበት መንገድ የጨዋታው ኮከብ አስብሎታል።
ሃላንድ በጭማሪ ስአት (91ኛው ደቂቃ) ያስቆጠራት የፍጹም ቅጣት ጎልም የስፐርሶችን ወደ ሻምፒዮንስ ሊጉ የመግባት ጥረት አምክኗል።
በተለይ የከተማ ተቀናቃኛቸውን ድል ሲጠባበቁ ለነበሩት የአርሰናል ደጋፊዎች ውጤቱ የዋንጫ ተስፋቸውን አጨልሟል።
ሲቲ ለአራተኛ ተከታታይ አመት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ቢቃረብም መድፈኞቹ የጠበበም ቢሆን እድል አላቸው።
የዘንድሮውን የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የመወሰን ሚናም በኤቨርተን እና ዌስትሃም ላይ ወድቋል።
የሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ 12 ስአት ሲደረጉ አርሰናል በኤምሬትስ የመርሲሳይዱን ክለብ ኤቨርተን ይገጥማል።
ሊጉን በ88 ነጥብ እየመራ የሚገኘው ሲቲ በበኩሉ በኢትሃድ ዌስትሃምን ያስተናግዳል።
መድፈኞቹ ከ20 አመት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ኤቨርተንን ማሸነፍና የሲቲን መሸነፍ አልያም አቻ መውጣት ይጠባበቃል።