የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች በ“ቪኤአር” ቀጣይ እጣፈንታ ዙሪያ በመጪው ሰኔ ወር ይወስናሉ
ወልቭስ ዳኞችን የሚያግዘው የቪዲዮ ቴክኖሎጂ ከቀጣዩ የውድድር አመት ጀምሮ ጥቅም ላይ እንዳይውል ጠይቋል
ስዊድን በደጋፊዎች ግጭት ምክንያት ቪኤአርን ባለፈው ወር ማገዷ ይታወሳል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከቀጣዩ የውድድር አመት በኋላ የ”ቪኤአር” ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እንዳይውል በመጪው ሰኔ ወር ውሳኔ ያሳልፋሉ።
ዳኞች ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያሳልፉ የሚያግዘው “ቪኤአር” በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከ2019 ጀምሮ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።
በ2023/24 የተስተናገዱ አከራካሪ ጉዳዮች ግን በቴክኖሎጂው ላይ ትችቶች እንዲበራከቱ አድርጓል።
ወልቭስም “ቪኤአር” ከ2024/25 የውድድር አመት ጀምሮ እንዲታገድ ለፕሪሚየር ሊጉ ጥያቄ ማስገባቱ ተገልጿል።
ክለቡ ቴክኖሎጂው የዳኞች ውሳኔ ትክክለኝነት ላይ በጎ አስተዋጽኦ እንዳለው ቢያምንም የጨዋታ ስሜትን እየጎዳ ነው ብሏል።
“ቪኤአር የደጋፊዎች እና እግርኳስ ትስስርን እየጎዳ ነው፤ የፕሪሚየር ሊጉን ብራንድም ዝቅ እያደረገው ነው” ሲል ቅሬራውን ገልጿል።
ቴክኖሎጂው በተለይ ጎል ከተቆጠረ በኋላ ስሜትን ከመግለጽ አንጻር የተጫዋቾችን ስነልቦና እየጎዳ መሆኑን የተለያዩ ክለቦች እና ደጋፊዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል።
በዳኞች የተላለፉ ውሳኔዎች አጠራጣሪ ሆነው በ”ቪኤአር” ሲታይ የሚወስደው ረጅም ጊዜም ተወዳጁን እግርኳስ ተፈጥሯዊ ውበት እየቀነሰው መሄዱንም ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
ቴክኖሎጂው ሜዳ ውስጥ ያሉትን ዳኞች ተአማኒነት እና ተቀባይነትም ጥያቄ ውስጥ መክተት መጀመሩና ዳኞችም ጭምር በአንዳንድ የቪኤአር ውሳኔዎች ላይ ደስተኛ አለመሆናቸውን ሲናገሩም ይደመጣል።
በአውሮፓ ተወዳጅ በሆነው ሊግ የቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ መዋል በወልቭስ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ክለቦችም ቅሬታን ሲያስነሳ ቆይቷል።
በመስከረም ወር የሊቨርፑሉ ልዊስ ዲያዝ በቶተንሃም ላይ ያስቆጠራት ጎል ከጨዋታ ውጭ ናት በሚል የተላለፈው አከራካሪ የቪኤአር ውሳኔን ጨምሮ በርካታ ክለቦች በአዲሱ ቴክኖሎጂ ላይ ቅሬታ አላቸው።
ኖቲንግሀም ፎረስትም ከኤቨርተን ጋር ሲጫወት ሶስት የፍጹም ቅጣት ምት ጥያቄዎችን መከልከሉን ማሳወቁ አይዘነጋም።
20 የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች በፈረንጆቹ ሰኔ 6 2024 በሚያደርጉት ጉባኤ ወልቭስ ባቀረበው ጥያቄ ላይ ድምጽ ይሰጣሉ ተብሏል።
ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ሶስት አራተኛው ይሁንታን ከሰጡትም “ቪኤአር” በቀጣዩ የውድድር አመት ጥቅም ላይ መዋሉ ያበቃለታል።
የሊጉ አመራሮች ግን ቅሬታዎቹን ቢቀበልም ቴክኖሎጂው እንዲቀጥል ይፈልጋል ነው የተባለው።
ስዊድን ባለፈው ወር ቪኤአር ጥቅም ላይ እንዳይውል በማገድ ከ30 የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አባላት ብቸኛዋ ሀገር መሆኗ ይታወሳል።
ስቶኮልም ከዚህ ውሳኔ ለመድረስም በቪኤአር ውሳኔ ምክንያት ደጋፊዎች ግጭት ውስጥ መግባታቸው በምክንያትነት ተጠቅሶ ነበር።