ኤርዶሃን የፍልስጤማውያንን ሰቆቃን የሚያባብስ የምዕራባውያን ድጋፍ ተቀባይነት የለውም አሉ
የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ በአንካራ ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ጋር ተወያይተዋል
አባስ በዛሬው እለት በቱርክ ፓርላማ በመገኘት በፍልስጤም ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ ያደርጋሉ
የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ በአንካራ ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ጋር ተወያዩ።
በዝግ የተካሄደው ምክክር “እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ እየፈጸመችው ባለው ጭፍጨፋ እና ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር” ብሏል የፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ጽህፈት ቤት።
እስራኤል በሃማስን የጥቅምት 7 ጥቃት ተከትሎ በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት አጥብቀው የሚቃወሙት ኤርዶሃን፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁንን ከአዶልፍ ሂትለር ጋር እስከማመሳሰል መድረሳቸው ይታወሳል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በሽብርተኛ ድርጅትነት የመዘገቡትን ሃማስም “የነጻነት ታጋይ" ነው በማለት ማወደሳቸውም አይዘነጋም።
ምዕራባውያን ሀገራት በእስራኤል ላይ ጫና ፈጥረው ጦርነቱን ከማስቆም ይልቅ ድጋፋቸውን መቀጠላቸውን ሲኮንኑ የቆዩት ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን፥ ከማህሙድ አባስ ጋር ሲወያዩም 40 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ህይወት አልፎ ዝምታን መርጠዋል ያሏቸውን ምዕራባውያን ኮንነዋል።
“እስራኤል ንጹሃንን መጨፍጨፏን ቀጥላለች፤ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና የስደተኞች መጠለያዎችንም እያፈራረሰች ነው፤ ፍልስጤማውያን ለረሃብና እርዛት መጋለጣቸው በቀጠለበት ሁኔታ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ዝምታን መምረጣቸው ተቀባይነት የለውም” ሲሉም ተደምጠዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሁሉም የንጹሃን ሞትና መፈናቀል የሚያሳስባቸው ሀገራት በተለይም የእስልምናው አለም በጋዛ በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥረታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንቱ ማህሙድ አባስ በአንካራ ከፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ጋር የመከሩት በሞስኮ ከፑቲን ጋር ከተነጋገሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
አባስ በዛሬው እለትም በቱርክ ፓርላማ ተገኝተው በፍልስጤም ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ እንደሚሰጡ የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።