ቱርክ ኔቶ ከእስራኤል ጋር ለመተባበር የሚያደርገውን ጥረት ትቃወማለች - ኤርዶሃን
ፕሬዝዳንቱ በዋሽንግተን በተካሄደው የኔቶ አመታዊ ጉባኤ በፍልስጤም ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ጥሪ አቅርበዋል
አንካራ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን በዲፕሎማሲያዊ ንግግር ለማስቆም ጥረቷን እንደምትቀጥልም ኤርዶሃን ተናግረዋል
ቱርክ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ከእስራኤል ጋር ትብብሩን መቀጠል አይችልም ስትል ተቃወመች።
ከባለፈው ማክሰኞች ጀምሮ በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የኔቶ አመታዊ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው ተቃውሟቸውን ያሰሙት።
“በፍልስጤም ሁሉን አካታች እና ዘላቂ ሰላም እስካልተረጋገጠ ድረስ ኔቶ ከእስራኤል ጋር የሚያደርገው ትብብር በቱርክ ተቀባይነት አይኖረውም” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በእስራኤል ላይ የሰላ ትችት የሚሰነዝሩት ኤርዶሃን 32 አባላት ያሉት ወታደራዊ ስብስብ ለቴል አቪቭ ድጋፍ ከማድረግ እንዲቆጠብ ነው የጠየቁት።
“ሽብርተኛው ሃማስ ሳይሆን ኔታንያሁ ነው” በሚለው ንግግራቸው የሚታወሱት የቱርኩ ፕሬዝዳንት፥ ዘጠኝ ወራት ያለፈውና ከ38 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ያለቁበት ጦርነት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
በየካቲት ወር 2022 የተጀመረውን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ ንግግር ለማስቆምም አንካራ ጥረቷን ትቀጥላለች ነው ያሉት።
ኤርዶሃን ከጎረቤት ሶሪያ ጋር ያለውን ውጥረት ለማርገብና ከደማስቆ ጋር ግንኙነታቸውን ለማደስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ሃካን ፊዳን የሶሪያውን ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ አግኝነው እንዲወያዩ ማዘዛቸውንም በዋሽንግተኑ መግለጫቸው አብራርተዋል።
ቱርክ ከአሜሪካ ለመግዛት ባቀደችው የኤፍ - 16 ተዋጊ ጄቶች ጉዳይም ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር እንደሚመክሩ ነው ያነሱት።
አንካራ ለስዊድን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ድጋፍ መስጠቷን ተከትሎ 23 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ኤፍ - 16 ጄቶችና መለዋወጫዎች ግዥ እንድትፈጽም ባለፈው መጋቢት ወር መፈቀዱ የሚታወስ ነው።
በፈረንጆቹ 1952 የኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ በ2017 ከሩሲያ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ኤስ - 400 የአየር መቃወሚያዎች መግዛቷ ከምዕራባውያን ጋር ግንኙነቷን አሻክሮት ቆይቷል።
የስዊድንን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ለመቀበል ያስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታም ከአሜሪካ ጋር ዳግም ግንኙነቷን እንድታድስ ማድረጉ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በኔቶ አመታዊ ጉባኤ የወታደራዊ ጥምረቱ አባላት አንካራ በሽብርተኞች ላይ የጀመረችውን ዘመቻ እንዲያግዟት ጠይቀዋል።
ኤርዶሃን በስም ባይጠቅሷቸውም የተወሰኑ የስብስቡ አባል ሀገራት ከዋይፒጂ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸውን ነው ያነሱት።
ከኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) ጋር ግንኙነት ያለው ዋይፒጂን በሽብርተኝነት የፈረጀችው ቱርክ፥ ምዕራባውያን አጋሮቿ እንደ ፒኬኬ ሁሉ ዋይፒጂን በሽብርተኝነት እንዲመዘግቡት ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቧን ሬውተርስ አስታውሷል።