ኔታንያሁን ከሂትለር የሚለየው ምንም የለም” - ኤርዶሃን
ኔታንያሁ በበኩላቸው፥ ፥ኩርዶችን የሚጨፈጭፈው ኤርዶሃን ስለሰብአዊነት የሚሰብክበት ሞራል የለውም” ብለዋል
ቱርክና እስራኤል የቃላት ጦርነት ውስጥ ቢገቡም የንግድ ግንኙነታቸው አልተቋረጠም
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከአዶልፍ ሂትለር ጋር አመሳስለዋቸዋል።
እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ እየፈጸመች ያለውን ጥቃት አይሁዳውያን በናዚዎች ከደረሰባቸው በደል ጋር ተመሳሳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባሏ ቱርክ እስራኤል በጋዛ በአየርና በምድር የምትፈጽመውን ጥቃት በተደጋጋሚ ስታወዝ ቆይታለች።
እስራኤልን “ሽብርተኛ ሀገር” አድርጋ መቁጠር የጀመረችው አንካራ ኔታንያሁን ጨምሮ በጋዛ የንጹሃንን ደም ያፈሰሱ የእስራኤል ባለስልጣናት በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲከሰሱም መጠየቋ ይታወሳል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እና በአጋሮቻቸው ላይ ተደጋጋሚ ትችት ሲያሰሙ የቆዩት ኤርዶሃን በዛሬው እለትም “ምዕራባውያን ለእስራኤል የጦር ወንጀል ተባባሪ ናቸው” ብለዋል።
“ስለሂትለር ጨካኝነት ደጋግመው ይናገራሉ፤ ከሂትለር በምን ትለያላችሁ? ተግባራችሁ ሂትለርን እንድንረሳው የሚያደርግ ነው፤ ኔታንያሁ እያደረገ ያለው ከሂትለር በምን ያንሳል?” ሲሉም ነው የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር እና ምዕራባውያኑን የወቀሱት።
“(ኔታንያሁ) ከሂትለር የበለጠ ሃብታም ነው፤ ከምዕራባውያን ድጋፍ ያገኛል፤ ማንኛውም አይነት ድጋፍ ከአሜሪካ ይደረግለታል፤ በዚህ ድጋፍ ምን አደረጉበት? ከ20 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ገደሉ” ነው ያሉት ኤርዶሃን።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለኤርዶሃን አስተያየት በሰጡት ምላሽ፥ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ለእስራኤል ስለሰብአዊነት የሰበኩ የመጨረሻው ሰው ናቸው ሲሉ ተሳልቀዋል።
“ኩርዶችን የጨፈጨፈውና አገዛዙን የተቃወሙ ጋዜጠኞችን በማሰር በአለም ክብረወሰን የያዘው ኤርዶሃን” እስራኤልን የመተቸት ሞራል የላቸውም የሚል መግለጫንም አውጥተዋል።
የቱርክና እስራኤል መሪዎች የቃላት ጦርነት ከጀመሩ ቢሰነባብቱም አንካራ ከቴል አቪቭ ጋር የንግድ ግንኙነቷን እስካሁን አላቋረጠችም።
ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እና እንደ ኢራን ካሉ ሀገራት ተቃውሞው የበረታባቸው ኤርዶሃን የቱርክና እስራኤል የንግድ ግንኙነት ከጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት በኋላ እየቀነሰ መሄዱን ከመግለጽ ውጭ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ስለማቋረጥ ያሉት ነገር የለም።