ፑቲን በፍልስጤማውያን ስቃይ ሞስኮ ከፍተኛ ህመም እንደሚሰማት ለአባስ ተናገሩ
ፑቲን ሞሶኮ በዩክሬን ጦርነት ብትወጠርም፣ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚካሄዱ ሁነቶች ትኩረት ትሰጣለች ብለዋል
የ88 አመቱ የፍልስጤም ፕሬዝደንት መሀሙድ ከባስ ሩሲያ የፍልስጤማውያን "የቅርብ ወዳጆች ከሆኑት አንዷ ነች" ብለዋል
ፑቲን በፍልስጤማውያን ስቃይ ሞስኮ ከፍተኛ ህመም እንደሚሰማት ለአባስ ተናገሩ።
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን በጉብኝት ላይ ለሚገኙት የፍልስጤሙ ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ ሞስኮ የህዝባቸው ስቃይ እንደሚያማት እና ነጻ ሀገር የመሆን ህልማቸውን ሙሉ በሙሉ እንደምትደግፍ በትናንትናው እለት ነግረዋቸዋል።
ፑቲን ሞሶኮ በዩክሬን ጦርነት ብትወጠርም፣ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚካሄዱ ሁነቶች ትኩረት ትሰጣለች ብለዋል።
ፕሬዝደንት ፑቲን ዩክሬን በምስራቅ ሩሲያ ድንበር ጥሳ እየፈጸመችው ስላለው እና ከ130ሺ በላይ ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ ስላስገደደው ጥቃት በቀጥታ አልተናገሩም።
"ሩሲያ ያለችበትን ሁኔታ ሁሉም ያውቃል። እንዳለመታደል ሆኖ፣ ሩሲያ እጇ ላይ ያለውን መሳሪያ ሁሉ በመጠቀም ህዝቧን እና ፍላጎታን መጠቀቅ አለባት። ነገርገን በመካከለኛው ምስራቅ እና በፍልስጤም እየተፈጠሩ ያሉ ክስቶችን ዝም ብለን አናይም" ብለዋል ፑቲን።
ፑቲን አክለውም "በርግጥ በፍልስጤም ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ስናይ ህመም እና ጭንቀት ይሰማናል" ሲሉ ተናግረዋል። ፑቲን ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ጥቃት በመፈጸም 1200 ሰዎችን መግደሉን እና 250 ሰዎችን አግቶ መውሰዱን ተከትሎ እስራኤላውያን በወሰደችው መጠነሰፊ ጥቃት 40ሺ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን አስታውሰዋል።
ሩሲያ ከእስራኤል እና ከፍልስጤም ጋር ለረጅም ጊዜ የቆየ መልካም ግንኙነት አላት። ነገርግን የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሞስኮ የሀማስ የልኡክ ቡድኖችን በማስተናገድ እስራኤልን ቅር አሰኝታለች።
የ88 አመቱ የፍልስጤም ፕሬዝደንት መሀሙድ ከባስ ሩሲያ የፍልስጤማውያን "የቅርብ ወዳጆች ከሆኑት አንዷ ነች" ብለዋል።
"በእናንተ(በሩሲያ) እንተማመናለን። ድጋፋችሁንም እያየን ነው" ሲሉ አክለዋል አባስ።
አባስ ድምጽን በድምጽ የመሻር (ቬቶ ፓወር) ያላት ሩሲያ አባል የሆነችበት የተመድ የጸጥታ ምክር ቤት እስራኤል በጋዛ እየወሰደችው ያለውን እርምጃ ማስቆም አለባት ብለዋል። ባለፈው ወር የአለምአቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት ዳኞች የእስራኤል የፍልስጤም ግዛቶችን የመውረረ እና የሰፈራ ቦታዎችን የማስፋፋት ተግባር ህገወጥ ነው የሚል ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወሳል።
በመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ የፈጠረው በተሳሳተ የአሜሪካ ፖሊሲ ምክንያት ነው የምትለው ሩሲያ ራሷን ገለልተኛ አድርጋ ታቀርባች።