ኤርዶጋን “በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ሁለት እውነተኛ መሪዎች ብቻ ናቸው ያሉት፤ እነሱም እኔና ፑቲን ነን” አሉ
ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን “ልምድ ያለው መሪ ለፖለቲካው መቀጠል በጣም ወሳኝ ነው” ብለዋል
የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልና መራሄ መንግስት ጄርሃርድ ሽሮደርን ምርጥ መሪዎች ነበሩ ብለዋል
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን “በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ሁለት እውነተኛ መሪዎች ብቻ ናቸው ያሉት፤ እነሱም እኔ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ናቸው” አሉ።
"አሁን በአለም ላይ ሁለት ልምድ ያላቸው መሪዎች እኔ እራሴ እና ቭላድሚር ፑቲን ነን፤ ይህንን ያልኩት ከሁለት አንዱ እኔ ስለሆንኩ አይደለም” ብለዋል ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን በንግግራቸው።
ነገር ግን “እኔ የ22 ዓመት ልምድ አለኝ” ያሉት ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን፤ ይህም “ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር የሚቀራረብ እና የረጅም ዓመት ልምድ በመሆኑ ነው” ብለዋል።
“አሁን ላይ ልምድ ያላቸው መሪዎች የሉም፤ የቀረነው ሁለታችን ብቻ ነን” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “በሁለታችን መካከል ያለው ንግግር አንዲቀጥል እንፈልጋለን” ሲሉም ተናግረዋል።
“ልምድ ያለው መሪ ለፖለቲካው መቀጠል በጣም ወሳኝ ነው” ያሉት ኤርዶጋን፤ “ልምድ ያለው መሪ ከሌለ ፖለቲካ ያበቃለታል፤ ለአብነትም መራሂተ መንግስት አንጌላ መርከል ከስልጣን ሲለቁ ነው የጀርመን ፖለቲካ ያበቃለት” ብለዋል።
የጀርመን የቀድሞ መራሄ መንግስት (ቻንስለር) ጄርሃርድ ሽሮደርን ለሌሎች ክብር ያላቸው መሪ እንደሆኑም የተናገሩት ኤርዶጋን፤ "ለእኛ የነበረው የአክብሮት ደረጃ ፈጽሞ የተለየ ነበር እና ጥሩ መሪ ነበር” ሲሉም ተናግረዋል።
ለምሳሌ “በታላቁ የረመዳን ወር ላይ የጀርመን የቀድሞ መራሄ መንግስት ጄርሃርድ ሽሮደርን እኛ የተቀመጥንበት ጠረጴዛ ላይ ቢራ አይጠጣም ነበር” ሲሉም የሚሰጡትን ክብር አንስተዋል።
“ጄርሃርድ ሽሮደርን ለእኛ ያለውን ክብር አሳይቷል፤ ከሽሮደርን ጋር አሁንም እንነጋገራለን፤ በተደጋጋሚም በቱርክ ጉብኝት ያደርጋል” ሲሉም አስታውቀዋል።