የአውሮፓ ህብረት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ቱርክ ህብረቱን መቀላቀል አትችልም ብሏል
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲጽ ጣይብ ኤርዶጋን አንካራ አስፈላጊ ከሆነ ከአውሮፓ ህብረት ልትለያይ ትችላለች ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት የአውሮፓ ህብረት ም/ቤት በቱርክ ላይ ስላወጣው ሪፖርት ተጠይቀው ነው።
በዚህ ሳምንት በጸደቀው ሪፖርት ቱርክ 27 አባላት ያሉትን ህብረት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ መቀላቀል አትችልም ብሏል።
የአውሮፓ ህብረት ከአንካራ ጋር የጎንዮሽና እውነታውን ያገናዘበ ግንኙነትን ለመፈለግ መዋቅር እንዲጤን ጥሪ አቅርቧል።
ቱርክ ላለፉት 24 ዓመታት የአውሮፓ ህብረትን ለመቀላቀል ይፋዊ እጩ ነበረች።
ሆኖም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአባልነት ንግግሮች ተስተጓጉለዋል። ለዚህም ህብረቱ የአንካራን የሰብዓዊ መብት አያያዝና የህግ የበላይነት እንዳሳሰበው ገልጿል።
ኤርዶጋን "የአውሮፓ ህብረት ከቱርክ ጋር ለመለያየት እየፈለገ ነው" ብለዋል።
ይህን ተከትሎም ሀገራቸው እርምጃ ትወስዳለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አስፈላጊ ከሆነም ከህብረቱ እንገነጠላለን በማለት ተናግረዋል።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአውሮፓ ም/ቤት ሪፖርትን መሠረተ ቢስ ውንጀላዎችን የያዘ ነው ብሎታል።
ሪፖርቱ ሀገሪቱ ላይ ጭፍን ጥላቻዎችን ያካተተ ነው ተብሏልም።