ሙስሊም የዓለም ሀገራት በፍልስጤማዊያን ጉዳይ እንዲተባበርም አሳስበዋል
የቱርክ ፕሬዝዳንት የእስራኤል ጉብኝታቸውን ሰረዙ።
ከ20 ቀናት በፊት ለፍስልጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ በእስራኤል ላይ ያልታሰበ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ በአካባቢው ጦርነት ተቀስቅሷል፡፡
እስካሁን የዓለም ዋነኛ የትኩረት አጀንዳ የሆነው ይህ ጦርነት መቋጫ ያልተገኘለት ሲሆን የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና ሌሎችም ሀገራት መሪዎች በእስራኤል ጉብኝት አድርገዋል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሀን እስራኤልን የመጎብኘት እቅድ የነበራቸው ቢሆንም መሰረዛቸው ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንቱ ጉብኝታቸውን የሰረዙት እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ እያደረሰችው ያለው ጥቃት መቀጠሉን ተከትሎ ነው።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ምዕራባዊያን እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ እያደረሰች ያለውን ጥቃት አለማውገዛቸውን ተችተዋል።
የሙስሊም ሀገራት በጋዛ ጉዳይ ትብብር እንዲያደርጉ የጠየቁት ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆምም አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው እስራኤል በጋዛ ጦሯን እንዳታሰማራ እና ለፍልስጤማዊያን ሰብዓዊ ድጋፍ እየተጓዘበት ያለው የራፋ ድንበር እንዳይዘጋ ብለዋል።
የእስራኤል- ሐማስ/ፍልስጤም/ ጦርነት ከ6 ሺህ በላይ ዜጎች ህይወታቸውን እንዲያጡ ያደረገ ሲሆን የተወሰኑ ሀገራት ከእስራኤል እና ከፍልስጤማዊያን ጎን ሙሆናቸውን በመናገር ላይ ናቸው።
የተወሰኑ ሀገራት ደግሞ ጦርነት ንጹሀን ዜጎች እንዲጎዱ አድርጓል በሚል ጦርነቱ እንዲቆም በመወትወት ላይ ይገኛሉ።