“ኔታንያሁ በጦር ወንጀል ተከሶ መቅረቡ አይቀርም”- ኤርዶሃን
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ለፍልስጤማውያን ህጻናት ፍጅት “ማየትም ሆነ መስማት የተሳናቸው ምዕራባውያን” ተባባሪ ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል
አንካራ የፍልስጤሙን ሃማስ እንደ ምዕራባውያን ሀገራት በሽብር አልፈረጀችም
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ እየፈጸሙት በሚገኙት የጦር ወንጀል በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መከሰሳቸው አይቀርም አሉየቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን።
ፕሬዝዳንቱ የእስላሚክ ትብብር ድርጅት ጉባኤ በኢስታንቡል ሲካሄድ ባደረጉት ንግግር፥ “ኔታንያሁ እንደ ሚሎሴቪች ሁሉ በጦር ወንጀል ይከሰሳል” ሲሉ ተደምጠዋል።
የቀድሞው የዩጎዝሊቪያ ፕሬዝዳንት ስሎቦዳን ሚሎሴቪች በዘ ሄግ በዘር ፍጅት፣ በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል እና በጦር ወንጀል መከሰሳቸው የሚታወስ ነው።
- ከቅዳሜ ወዲህ በጋዛ ከ800 በላይ ፍሊስጤማውያን መገደላቸው ተገለጸ
- በጋዛ ተኩስ አቁም የሚደረግ ከሆነ ቱርክ መልሶ የመገንባት ፍላጎት እንዳላት ኤርዶጋን ተናገሩ
ኤርዶሃን በንግግራቸው “ማየትም ሆነ መስማት የተሳናቸው” ሲሉ የገለጿቸውን ምዕራባውያን ሀገራት የእስራኤል የጦር ወንጀል ተባባሪ ናቸው ብለዋል።
ምዕራባውያኑ እስራኤል “ህጻናትን ያለ ርህራሄ እንድትገድል ያልተገደበ ድጋፍ ማድረጋቸው”ንም ተቃውመዋል።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ለንጹሃን ሞት ሃማስን እንደምክንያት የሚያቀርቡ ከሰብአዊነት የተቆራረጡ ናቸው ሲሉም ወቅሰዋል።
መላው አለምን በማይወክል መንገድ ለአምስት ሀገራት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት የሰጠው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት የፍልስጤማውያንን ሰቆቃ ማስቆም አለመቻሉን በመጥቀስም “ፈጣን ሪፎርም ያስፈልገዋል” ብለዋል።
የኔቶ አባሏ አንካራ እንደሌሎች የምዕራባውያን ሀገራት ሃማስን በሽብርተኝነት አትፈርጅም፤ ቡድኑ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ከጀመረ አንስቶም ስታወግዘው አልታየም።
ለፍልስጤማውያን ነጻ ሀገር የመመስረት የአመታት ትግል ድጋፍ እንዳላት የምትገልጸው ቱርክ “ አሸባሪው ኔታንያሁ እንጂ ሃማስ አይደለም” በሚልም ለቡድኑ ድጋፏን መግለጿ ይታወሳል።
አንካራ የአረብና ሙስሊም ሀገራትን በማስተባበርም የጋዛ ድብደባ እንዲቆም ጥረት ማድረጓን እንደምትቀጥል ኤርዶሃን ተናግረዋል።