ኤርትራ የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ጽ/ቤት ዋና ፀሀፊ ማርክ ሎውኮክን ወቅሳለች
የኤርትራ መንግስት በትግራይ ሰብዓዊ ተደራሽነትን በጭራሽ አላደናቀፍኩም ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የኤርትራ አምባሳደር ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ቀናት የተመድ ፀጥታው ም/ቤት የትግራይ ክልል አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተ መደበኛ ያልሆነ ውይይት ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡በዚህ ውይይት የተ.መ.ድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ጽ/ቤት ዋና ፀሀፊ ማርክ ሎውኮክ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ስራ አስፈፃሚ ዴቪድ ቤስሌይ ተጋብዘው ለአባላቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በውይይቱ የትግራይ አሁናዊ ሁኔታ ተነስቶ በኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች አማካኝነት ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ ይሁን እንጂ “ከሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትና ረሀብን እንደ መሳርያ” ከመጠቀም ጋር ተያይዞ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ስሟን በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረው ኤርትራ፤ ሳትጋበዝ የውይይቱን አጀንዳ መሆኗ የኤርትራ መንግስት በውይይቱ ላይ ያለው ተቃውሞ እንዲገልጽ መገደዱን አስታውቀዋል፡፡
ኒውዮርክን ማእከሉን ያደረገው በተመድ የኤርትራ ቋሚ ሚስዮን በጉዳዩ ላይ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
ውይይቱ ኤርትራ ያልተጋበዘችበት፤ጉዳዩ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መሆኑ ግልፅ ስለሆነ ነው በማለት የጀመረው መግለጫው፤ ይሁን እንጂ የወጣው መግለጫም ሆነ በሚድያ አውታሮች ሲገለጽ የነበረው የውይይት መድረኩ በኤርትራ ላይ ያልተመሰረቱ ክሶችን እንደገና ለማደስ እንደ ሌላ አጋጣሚ ጥቅም ላይ መዋሉን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ይህ በግልጽ ባይቀመጥና በአጀንዳዎቹ ላይ ባይገለጽም እንዲሁም ኤርትራ በተነሱት ጉዳዮች ላይ ያላትን ኃሳብ እንድታቀረብ ዕድል ባይሰጣትም ፤ኤርትራ በዚህ ውይይት ላይ ጥቅም ላይ የዋለውን አሳዛኝ እና ግልጽ ያልሆነ የአሰራር ዘዴ እንደምትቃወም አስታውቀዋል የሚስዮኑ መግለጫ፡፡
መግለጫው “ኤርትራ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ተደራሽነትን በጭራሽ አላደናቀፈችም ፤ ኤርትራ አሁን ላይ “ምግብን እንደ ጦር መሣሪያነት” ልትጠቀም ይቅርና በእነዛ የ1998 እስከ 2000 ጦርነት ወቅቶች በነበሩ ጨለማ ቀናት እንኳን አልተጠቀመችም” ሲልም አክለዋል፡፡
የጠፋውን የህወሓትን ቡድን ከፍተኛ ወንጀሎች ለማቃለል ሲባል ኤርትራን ጥፋተኛ ለማድረግ የሚደረገውን ተከታታይ ዘመቻ ኤርትራ አጥብቃ እንደምትቃወምም መግለጫው አመላክተዋል፡፡
በተ.መ.ድ የኤርትራ ተወካይ ሶፍያ ተስፋማርያም በፈረንጆቹ ሚያዝያ 16 ለፀጥታው ም/ቤት “… ሌሎች ሀገሮች በተመሳሳይ ሁኔታ ራሰቸውን ለመከላከል እንዲወስዱ የተገደዱባቸው የመከላከያ እርምጃዎች እኛን ለመወንጀል መሞከራቸው በእውነት በጣም እናዝናለን ፡፡ በኤርትራዊ ወታደሮች ላይ የቀረቡት የአስገድዶ መደፈር እና ሌሎች ወንጀሎች ክፋቶች ብቻ ሳይሆኑ በህዝባችን ባህል እና ታሪክ ላይም ከባድ ጥቃት ናቸው ….” ማለታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የሚስዮኑ መግለጫ በእነዚህ ወሳኝ ጊዜያት ፣ ዓለም አቀፍ ህጎችን እና የቀጣናው ሀገራት ሉዓላዊነትን በመጣስ ተገቢ፤ ባልሆኑ ጣልቃ ገብነቶች እና በማስፈራራት ተጨማሪ ግጭቶችን እና አለመረጋጋትን ማነሳሳት በማንኛውም ሽፋን ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡
በውይይቱ የተወሰኑ ኃይሎች በኤርትራ ላይ ያነሷቸው መሠረተ ቢስ ክሶች ፤ ሌሎች የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለማራመድ የሚገፉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
መግለጫው ተሰናባቹ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ጽ/ቤት /ኦቻ/ሃላፊው ቀውሱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እየሰነዘሩዋቸው ያሉ ውንጀላዎችና አስታያየቶች ማስረጃ አልባ ክሶችን ናቸው ስለዚህም ኤርትራ አትቀበላቸውም ሲልም አስምሮበታል፡፡
ኤርትራ የኦቻ ኃላፊው የሚያቀርቡት መረጃ የተዛባ ነው ይህም የተሰጣቸውን ተልእኮ እና የዓለም አቀፍ ሲቪል ሰርቪስነት አደጋ ላይ የጣለ ነው ስትል በሚያዝያ ወር መጨረሻወቹ አከባቢ ለተ.መ.ድ ዋና ጸሀፊው አንቶንዮ ጉተሬዝ አብየቱታ ማቅረቧ የሚታወስ ነው፡፡