የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኤርትራ ወታደሮች በኦሮሚያ ክልል አሉ ስለሚባለው ጉዳይ “መረጃ የለኝም” አለ
ኦነግ እና የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የኤርትራ ወታደሮች በኦሮሚያ ክልል የተለያ አካባቢዎች ውስጥ ተስተውለዋል ብለዋል
“በትግራይ 350 ሺህ ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል” በሚል የወጣው መረጃመ ሀሰት እንደሆነ ሚኒስቴሩ ገልጿዋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አማባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው እለት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ላይም የኤርትራ ወታደሮች በምእራብ ኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ ዞኖች እና በደቡብ ኦሮሚያ ውስጥ አሉ ስለሚባለው ጉዳይ ጥያቄ ቀርቦላቸው “መረጃ የለኝም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ከሰሞኑ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የኤርትራ ወታደሮች በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ ተስተውለዋል ሲሉ መዘገባቸው ይታወሳል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ከ5 ቀናት በፊት ባወጣው መረጃ የኤርትራ ወታደሮች በኦሮሚያ ክልል በተለይም በቦረና ዞን ነጌሌ ከተማ አካባቢ እንዲሁም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አባይ ጮመን በሚባል ስፍራ መታየታቸውን አስታውቋል።
ኦነግ የኤርትራ ወታደሮች ናቸው ያላቸው ግለሰቦች “ሁሉም አፋን ኦሮሞ ቋንቋን የማይችሉ እና የተወሰኑት ብቻ አማርኛ ቋንቋ የሚችሉ ናቸው” ብሏል።
ይሁንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አማባሳደር ዲና ሙፍቱ “የኤርትራ ወታደሮች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ታይተዋል ስለመባሉ ምንም መረጃ የለኝም” ብለዋል።
አማባሳደር ዲና አክለውም የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል መውጣት መጀመራቸውን ገልጸው ፣ ይህንንም መከላከያ ሚኒስቴር ማረጋገጡን አስታውሰዋል።
ትግራይ ክልል ከሚገኙ የኤርትራ ወታደሮች ምን ያክሉ ወጡ? መቼ ሙሉ በሙሉ ይወጣሉ? የሚለውን በተመለከተ “ሙሉ መረጃ የለኝም” ሲሉ መልሰዋል።
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር (NATO) በትግራይ ክልል ካለው ችግር ጋር በተያያዘ “ኢትዮጵያን ለመውረር ተዘጋጅቷል” በሚለው ላይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ እንደሌለው በመጠቆም፤ “ኢትዮጵያ ከሁሉም የኔቶ አባላት ጋር መልካም ግንኙነት ነው ያላት፤ ይህንን ያደርጋሉ የሚል እምነት የለኝም” በሚል የራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።
“በትግራይ 350 ሺህ ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል” በሚል ይፋ ያልሆነ የተባበሩት መንግስታት ጥናትን ዋቢ በማድረግ የወጣው መረጃ ትክክል እንዳልሆነ አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ “ረሃብ ተከስቷል ለማለት የተቀመጡ መስፈርቶች አሉ፤ አሁን በትግራይ ባለው ሁኔታ ከ90 በመቶ በላይ የክልሉ ነዋሪ ሰብዓዊ ድጋፍ አግኝቷል” ብለዋል፡፡ ለቀጣይ የእርሻ ስራም 70 በመቶ ለግብርና ስራ የሚውል መሬት ለእርሻ ስራ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው በዚህ ሁኔታ ረሃብ ይከሰታል የሚለው ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል።