በትግራይ ግጭት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞች ያሉበት እንደማይታወቅ ተ.መ.ድ ገለጸ
ከነዚህ ስደተኞች መካከል 8 ሺ ያህሉ ወደ ማይ ዓይኒና ዓዲ ሓሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች መመለሳቸውን ዩኤን ኤች ሲአር ቃል አቀባይ ተናግረዋል
መውደማቸው በተገለጸው የሕፃፅና ሽመልባ መጠለያ ጣቢያዎች 20 ሺ ገደማ ኤርትራውያን ስደተኞች ይኖሩ እንደነበር ይነገራል
በትግራይ ግጭት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞች ያሉበት እንደማይታወቅ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን /ዩ ኤን ኤች ሲአር/ አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ግጭቱን ተከትሎ በክልሉ በሚገኙ ሕፃፅ፣ ሽመልባ፣ ዓዲ ሓሩሽ እና ማይ ዓይኒ መጠለያ ጣቢያዎች ይኖሩ የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ሁኔታን የተመለከተ ግምገማ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ከአል-ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ኤሊዛቤት አርንስዶርፍ በግጭቱ ምክንያት ሁሉም የመገናኛ ዘዴዎች በመቋረጣቸው ኮሚሽኑ ስደተኞቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ተቸግሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከተወሰኑ ወራት በኋላ ኮሚሽኑ “በማይ ዓይኒና ዓዲ ሓሩሽ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች” የነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች የመድረስ እድል ማግኘቱን የሚናገሩት ቃል አቀባይዋ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ የድንገተኛ ጊዜ መጠለያዎችን ከመገንባት ባሻገር የውሀ አቅርቦት፣ የጥበቃ ተግባራት እንዲሁም የምግብ እርዳታ ስርጭት መጀመሩንና ይህ ይበልጥ ለማስፋት ኮሚሽኑ ከስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ሆኖም እስካሳለፍነው መጋቢት ድረስ ሕፃፅና ሽመልባ መጠለያ ጣቢያዎች ለመድረስ ተቸግረን ነበር ብለዋል ቃል አቀባይዋ ኤሊዛቤት፤ ከወራት በኋላ በተቀሩት ካምፖች ለመድረስ ቢቻልም የተከሰተው ነገር አሳዛኝ እንደነበር በመጠቆም፡፡
“ያየነው ሁሉ ቀደም ብሎ ሪፖርት ሲደረግልን የነበረው ነው፤ ሁለቱም ካምፖች ወድመዋል፣ ተዘርፈዋል ፣ ባዶ ናቸው፣ በውስጥ የነበሩ የኤርትራ ስደተኞችም ካምፖቹን ለቀው እንዲሰደዱ ተገደዋል፣ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መበታተናቸውንም አረጋግጠናል” በማለትም ነበር በመጠልያ ካምፖች ላይ የደረሰውን አደጋ የገለፁት ቃል አቀባይዋ፡፡
በወደሙት የሕፃፅና ሽመልባ ጣቢያዎች 20ሺ ስደተኞች ነበሩም ብለዋል፡፡
ከነዚህ መካከል በግላቸው፣ በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ እንዲሁም በኮሚሽኑ ትብብር ወደ ማይ ዓይኒና ዓዲ ሓሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች 8 ሺ ገደማ ስደተኞች መመለሳቸውንም ነው ቃል አቀባይዋ የገለጹት፡፡
ሆኖም ቀሪዎቹ አሁንም አዲስ አበባ፣ ዓፋር፣ መቀሌና አዲግራትን ወደመሳሰሉ የተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ተበታትነው እንደሚገኙም አስቀምጠዋል፡፡
ኮሚሽኑ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በአዲስ አበባ ያሉትን ኤርትራውያን ስደተኞች እየመዘገበና ያሉበትን ሁኔታ እየገመገመ እንደሆነም ነው ኤሊዛቤት አርንስዶርፍ የተናገሩት፡፡
ቃል አቀባይዋ የኤርትራውን ስደተኞች ሁኔታና ያሉበት ቦታ ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ሊገኙ ያልቻሉ በርካታ ኤርትራውያን እንዳሉ ግን አልሸሸጉም፡፡
“ልናገኝ ያልቻልናቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞች አሉ”ም ነው ያሉት ቃል አቀባይዋ ኤሊዛቤት፡፡
ቃል አቀባይዋ በትግራይ ግጭት ያሉ ተዋናዮች ለሰብዓዊ መርሆች ተገዢ እንዲሆኑና ለንጹሀን ማለትም ለስደተኞችና ተፈናቃዮች ደህንነት ቅድሚያ እንዲሰጡም አሳስቧል፡፡
በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ከ96ሺ በላይ የኤርትራ ስደተኞች በተለያዩ መጠልያ ካምፖች ተጠለው ይኖሩ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
አል ዐይን ተበታትነዋል የተባሉትን ኤርትራውያን ስደተኞች ጉዳይ በተመለከተ የመንግስትን ምላሽ ለማወቅ እና ከስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ተጨማሪ መረጃን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡