ኤርትራ በኮሮና ምክንያት በትራንሰፖርት አግልግሎት ላይ ጥላ የነበረውን እገዳ “በከፊል” አነሳች
የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል የተጀመረው ከፊል እንቅስቃሴ፡" ሁሉም የመከላከልና የክትትል መመሪያዎች" ያሟላ ነው ብለዋል
በኤርትራ እስካሁን ድረስ 3,208 ሰዎች በኮሮና መያዛቸውንና ከተያዙት ውስጥ 9 ሰዎች መሞታቸውን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ገልጸዋል
በኤርትራ ለአንድ አመት ያክል ተቋርጦ የነበረው የህዝብ ትራንስፓርት አገልግሎት "በከፊል" መጀመሩን የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
የማስታወቂያ ሚኒሰትሩ የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገፃቸው እንዳሰፈሩት ከሆነ፤ የትራንሰፖርት አገልግሎቱ የተፈቀደው በከተሞች እንዲሁም ከከተሞች ወደ ከተሞች ለሚደረግ ጉዞ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
"ከትምህርት ቤቶች መከፈት ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በከፊል ተጀምረዋል፡፡ አውቶብሶችም በከተሞች እንዲሁም ወደ ተመረጡ መስመሮችና የተለያዩ ከተሞች የሚንቀሳቀሱ ይሆናል"ም ነው ያሉት የዜና ሚኒሰትሩ የማነ ገ/መስቀል።
የተጀመረው ከፊል እንቅስቃሴ፡" ሁሉም የመከላከልና የክትትል መመሪያዎችን" ያሟላ ይሆናልም ብለዋል ሚኒሰትሩ የማነ ገ/መስቀል።
መንግስት ከአመት በላይ ተዘግተው የቆዩትን ትምህርት ቤቶች ከመጪው ሀሙስ ሚያዝያ 1 ጀምሮ እንደሚከፈቱ ከውሳኔ መድረሱ ይታወሳል፡፡
ከባለፈው አመት መጋቢት ወር አንስቶ በኤርትራ ተጥሎ የቆየው እገዳ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖምያዊ ቀውስ ማስከተሉም ይነገራል፡፡
ምንም እንኳን ኤርትራ ዝቅተኛ የኮሮና ቫይረስ ሰለባዎች ያላት ሀገር ብትሆንም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የቫይረሱ ባህርይ እያደገ መምጣቱን ነው ሚኒስቴሩ መረጃ የሚያመላክተው፡፡
እስካሁን ድረስ 3,208 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውንና 9 ለህልፍት መዳረጋቸውንም መረጃው ያመላክታል፡፡