ጠ/ሚ ዐቢይ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ግዛት እንደሚገኙ ከገለጹ ከሁለት ቀናት በኋላ አስመራ ገቡ
በአክሱም ከተማ ከአንድ መቶ በላይ ሲቪል ሰዎች በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን ኢሰመኮ መግለጹ ይታወሳል
መሪዎቹ በትግራይ ክልል በኤርትራ ወታደሮች ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጉዳይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፣ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ግዛት እንደሚገኙ ከገለጹ ከሁለት ቀናት በኋላ ፣ ዛሬ ከሰዓት አስመራ ከተማ መግባታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል አስታውቀዋል፡፡
አቶ የማነ በትዊተር ገጻቸው እንዳገለጹት ጠቅላይ ሚነስትሩ እና ልዑካቸው አስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፍወርቂ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ ወደ ኤርትራ መግባታቸው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በይፋ አልተገለጸም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ፣ የመከላከያ ሠራዊት በሕወሓት ኃይል መጠቃቱን ተከትሎ ወደኤርትራ ላቀኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች ስለተደረገላቸው እንክብካቤ የኤርትራ ሕዝብ እና መንግሥትን ማመስገናቸው ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል የኤርትራ መንግስት ከሕወሓት ኃይል ጥቃት ሊሰነዘርብኝ ይችላል የሚል የብሔራዊ ደህንነት ስጋት እንዳለበት በመጥቀስ የሀገሪቱን ወታደሮች በድንበር አካባቢ በሚገኙ የኢትዮጵያ ምሽጎች ማስፈሩን እንደገለጸላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ተመልሶ ምሽጉን ከተረከበ የኤርትራ ጦር ወዲያውኑ እንደሚወጣም ኤርትራ መግለጿን ጠቁመዋል፡፡ በኤርትራ ወታደሮች ተፈጽሟል ከሚባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ደግሞ የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ ግዛት እየተንቀሳቀሰ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተቀባይነት እንደሌለውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡ የኤርትራ ሰራዊት በትግራይ ክልል “በሴቶች ላይ ጥቃቶችን ፈጽሟል የመባሉን ሪፖርት ለኤርትራ መንግስት አቅርበን የኤርትራ መንግስትም ችግሩ ካለ እርምጃ እንወስዳለን ብሏል“ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው ነበር፡፡
የሁለቱ ሀገራት መንግስታት በነዚህ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ ስለመስማማታቸውም በወቅቱ አንስተዋል፡፡
በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤርትራ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ ፣ በዋናነትበትግራይ ክልል በሚገኘው የኤርትራ ጦር እና ተፈጸሙ በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ግዛት ለቆ እንዲወጣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡ ይህን ጨምሮ በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት ከተለያዩ አካላት የሚደረግባቸው ጫና ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ባወጣው መግለጫ በተለይም ከኅዳር 19 እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በነበሩት ሁለት ቀናት በኤርትራ ወታደሮች"ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደተፈጸመ" ይፋ አድርጓል። ከአንድ መቶ በላይ ሲቪል ሰዎች በወቅቱ በአክሱም ከተማ በነበሩ የኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ባለፈ በሌሎች የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ይመክራሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡