“ቀጣናው ችግሮችን በራሱ እንዲፈታ ከማገዝ ይልቅ ህወሓትን ለመታደግ እየሰራ ይገኛል” ስትልም ነው ህብረቱን የወቀሰችው
ኤርትራ የአውሮፓ ሕብረትን የማዕቀብ ውሳኔ ተቃወመች፡፡
ውሳኔውን የተመለከተ መግለጫን ያወጣው የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ህብረቱ ተፈጽመዋል ካላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ በኤርትራ ብሔራዊ ደኅንነት መስሪያ ቤት ላይ ያሳለፈው የማዕቀብ ውሳኔ ተገቢነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡
መግለጫው ህብረቱ ኤርትራን በዚህ መልኩ ሊመለከት የሚችልበትና ለዚህ ውሳኔ የሚያበቃው “የሞራልም ሆነ የህግ ልዕልና” እንደሌለው በመጠቆም ውሳኔውን “መሰረተ ቢስ” ሲል አጣጥሏል፡፡
ህብረቱ “ቀጣናው (ምስራቅ አፍሪካ) ችግሮችን በራሱ እንዲፈታ ከማገዝ ይልቅ ህወሓትን ለመታደግ እየሰራ ይገኛል” ሲልም ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው የወቀሰው፡፡
ኤርትራን እንዲህ ባለ መንገድ ዒላማ ማድረጉ በዋናነት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ባለው ግንኙነት “ሽብልቅ ለመቀርቀር” በማሰብ እንደሆነም ነው መግለጫው ያተተው፡፡
ዛሬ በቤልጂዬም ብራሰልስ መካሄድ በጀመረው የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባዔ ህብረቱ ኤርትራን ጨምሮ በምያንማር እና ቻይና ላይ ማዕቀብ መጣሉ የሚታወስ ነው፡፡
ቻይና በ11 የህብረቱ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ማዕቀብ በመጣል የአጸፋ ምላሽ መስጠቷም ተሰምቷል፡፡