“ዶናልድ ትራምፕ ዳግም የተመረጡት ሰላም ለዓለም በጣም አስፈላጊና ወሳኝ በሆነ ጊዜ ነው” ፕሬዝዳንት ኢሳያስ
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የትራምፕ መመረጥ በኤርትራና በአሜሪካ መካከል አዲስ የትብብር ምዕራፍ ይከፍታል ብለዋል
የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለዶናልድ ትራምፕ የደስታ መልእክት አስተላልፈዋል
የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ “ዶናልድ ትራምፕ ዳግም የተመረጡት ሰላም ለዓለም በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ጊዜ ነው” አሉ።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዶናልድ ትራምፕ 47ኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን ዳግም መመረጣቸውን ተከትሎ የደስታ መልእክት ማስተላፋቸውን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል አስታውቀዋል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በመልእከታቸው፤ የትራምፕ ምርጫ “ዓለም አቀፍ ሰላም ከምንጊዜውም በላይ እጅግ አስፈላጊ በሆነበት በጣም ወሳኝ ወቅት ላይ ነው” ብለዋል
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አክለውም “በዚህ ወሳኝ ዓላማ ላይ በያዙት አቋም ላይ ስኬታማ እንዲሆኑ መልካም ምኞታችንን እእንገልጻለን”ማለታቸውንም ከማስታወቂያ ሚኒስትሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የፕሬዝዳንት ትራምፕ ዳግም መመረጣቸው በኤርትራ እና በአሜሪካ መካከል አዲስ ፍሬያማ እና ገንቢ የትብብር ምዕራፍ ይከፍታል" ብለው እንደሚያምኑም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ገልጸዋል።
ዶናልድ ትራምፕ 47ኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን ዳግም መመረጣቸውን ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ደስታውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ከነዚህ መካከልም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) አንዱ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ስላሸነፉ እንኳን ደስ አለዎት፣ ወደ መሪነት እንኳን ድጋሚ መጡ አብረን እንደምንሰራ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ለዶናልድ ትራምፕ እና ባለቤታቸው እንኳን ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ተመለሱ ሲሉ በኤክስ አካውንታቸው ላይ ጽፈዋል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ኤልሳልቫዶር ፕሬዝዳንት ናይብ በክሌ፣ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ፣የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ኦርባን፣የስዊድን፣ ዴንማርክ ፣ጣልያን፣ ሆላንድ እና ሌሎችም ሀገራት መሪዎች የእንኳን ደስ ለዎት መልዕክታቸውን ለዶናልድ ትራምፕ ልከዋል።
የዩክሬን እና ሩሲያን ጦርነት በተመረጡ በማግስቱ እንደሚስቆሙ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ ከፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ደርሷቸዋል።