“የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ትራምፕ የገቡትን ቃል ተግባራዊነት ጊዜ ያሳየናል” -ሞስኮ
ከፍተኛ የሩሲያ ባለስልጣናት ትራምፕ እንዳሰቡት የዩክሬንን ጦርነት ማስቆም ቀላል እንደማይሆን በተደጋጋሚ ተናግረዋል
ዩክሬን በትራምፕ መመረጥ ከአሜሪካ የሚደረግላት ወታደራዊ ድጋፍ ሊቀንስ እንደሚችል ስጋት ውስጥ ትገኛለች
ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በመረጣቸው ዙርያ ሩሲያ ጥንቃቄ የተሞላበት አስተያየት ሰጥታለች፡፡
ቻይናን ጨምሮ የተለያዩ የአለም ሀገራት የሪፐብሊካኑ ዕጩ በማሸነፋቸው የእንኳን ደስ አሎዎት መልዕክት ሲያስተላለፉ የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እስካሁን ዝምታን መርጠዋል፡፡
የክሪሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ፑቲን የእንኳን ደስ አሎዎት መልዕክት ለማስተላለፍ በመወሰናቸው ላይ እርግጠኛ አይደለሁም ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን ተመራጩ ፕሬዝዳንት በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት የዩከሬንን ጦርነት ለማስቆም የገቡት ቃል ተፈጻሚነት በጊዜ የሚታይ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “እያወራን ያለነው በሀገራችን ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጦርነት ባወጀች ወዳጅ ስላለሆነች ሀገር መሆኑን መዘንጋት የለብንም” ብለዋል፡፡
“ለዚህ ግጭት መቋጨት የአሜሪካ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን በተደጋጋሚ ተናግረናል” ያሉት ቃል አቀባዩ “ይህ በአንድ ጀንበር ሊከናወን አይችልም። አሜሪካ ጠብ አጫሪ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን ትቀይራለች? ከጥር ወር በዓለ ሲመት በኋላ እንመለከታለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ በበኩሉ ሞስኮ አዲስ ከተመረጠው አስተዳደር ጋር የሩሲያን ጥቅም እና ፍላጎት ባከበረ መልኩ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ገልጿል፡፡
በ1962 በኩባ የሚሳይል ቀውስ ምክንያት አሜሪካ እና ሶቭየት ህብረት ወደ ኒዩክሌር ጦርነት ተቃርበው ከነበሩበት አጋጣሚ በኋላ በዩክሬን ጦርነት የተነሳ ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ትራምፕ አሸናፊነታቸውን ካወጁ በኋላ የመልካም ምኞታቸውን ከገለጹ የአለም መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ፕሬዝደንት ዘለንስኪ “በትራምፕ ዘመን ጠንካራ አሜሪካን እንደምንመለከት ተስፋ አድርጋለሁ” ብለዋል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው ለኪቪ በሚደረገው ወታደራዊ ድጋፍ ላይ በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ያሰሙት ተመራጩ ፕሬዝዳንት የድጋፍ ቅነሳ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ዩክሬን ሰግታለች፡፡
ትራምፕ ምንም እንኳን ጦርነቱን ለማስቆም ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም በሩስያ ፍላጎት እና ቅድመ ሁኔታ ላይ ተመርኩዘው ድርድሩን እንደማያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ በሩስያ የተያዙባት ግዛቶች እስካልተመለሱ ድረስ ከሞስኮ ጋር ለውይይት ጠረጴዛ አልከብም በሚለው አቋሟ ጸንታለች።
በአሁኑ ወቅትም በሰሜን ዩክሬን እና ሌሎች የጦር ግንባሮች ሩሲያ በተደራጀ ትጥቅ እና ጦር ከፍተኛ ውግያ መክፈቷን ዘገባው አክሏል፡፡
ከወታደራዊ ድጋፍ ጋር በተገናኝ የትራምፕ መመረጥ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመምከር ጀርመን ፈረንሳይ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ቀጠሮ ይዘዋል፡፡