ኤርትራ “የተሳሳተ ሪፖርት አውጥተዋል”ያለቻቸውን የተመድ ኤጄንሲዎች ተወካዮች አነጋገረች
በተመድ የኤርትራ አምባሳደር ሶፊያ የቀረቡትን ሪፖርቶች ተቃውመዋል
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የተመድ ኤርትራን የተመለከቱ የተሳሳቱ ሪፖርቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው ገለጹ
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መቀመጫቸው በኤርትራ ያደረጉትን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ሬዚደንት አስተባባሪንና የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮ ተወካዮችን ጠርቶ ማነጋገሩን የማስታወቅያ ሚኒስትሩ የማነ ገ/መስቀል በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡
ሚኒስትር የማነ “ከህወሐት ጋር ስውር ትስስር ያለቸውን ምንጮች መሰረት በማድረግ በተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮ እና ሌሎች የተመድ ኤጀንሲዎች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እንዲሁም እየወጡ የሚገኙ ሪፐርቶች ኤርትራ እንደምትቃወም ለተወካዮቹ ተነግሯቸዋል”ም ብለዋል፡፡
በትላንትናው ዕለት በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክርቤት ኤርትራን በማስመለከት ምላሽ የሰጡት፤ በምክር ቤቱ የኤርትራ አምባሰደርና ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ሶፍያ ተስፋማርያም የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ዘርፍ "በተደጋጋሚ ከተሰጠው ድርሻ ባሻገር በመሄድ ተቀባይነት የሌለው ገንቢ ያልሆነ ተግባራት ውስጥ ገብቷል" ሲሉ መክሰሳቸው የሚታወስ ነው።
በምክርቤቱ ስብሰባ የአሜሪካ መልዕክተኛ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድም የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ በአስገድዶ መድፈርና ፆታዊ ጥቃት አድርሰዋል የሚል ክስ አቅርበዋል፤መወጣት አለባቸውም ብለዋል፡፡
ነገርግን አምባሳደር ሶፊያ ይህን ክስ እንደማይቀበሉት ለተመድ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡