የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ በመውጣት ላይ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ
የቡድን 7 ሀገራት በመግለጫቸው አንገብጋቢ ለሆኑ ጉዳዮች ትኩረት እንዳልሰጡ ሚኒስቴሩ ገልጿል
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለ ጂ7 ሀገራት መግለጫ ምላሽ ሰጥቷል
የቡድን 7 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ፣ ከሁለት ቀናት በፊት በጋራ ባወጡት መግለጫ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የኤርትራ ወታደሮች በፍጥነት እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኢትዮጵያ እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቡድን 7 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መግለጫ በሰጠው ምላሽ ፣ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ግዛት በመውጣት ላይ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ በመግለጫው ፣ “ባለፈው ሳምንት እንደተገለጸው በሕወሓት ቀስቃሽነት ድንበር አቋርጠው የገቡት የኤርትራ ወታደሮች አሁን ለቀው መውጣት የጀመሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይልም ብሔራዊ ድንበሩን በመቆጣጠር ላይ ይገኛል” ብሏል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር የክልሉን የአስተዳደር መዋቅር ወደ ተሟላ አሠራር እንዲመለስ ለማድረግ “ያለመታከት እየሰራ” እንደሚገኝም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
የሕግ ማስከበር እርምጃዎቹ በስኬት ወደ መጠናቀቅ ከደረሱ በኋላ ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ ለመቅረፍ ጥረቱን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከፍተኛ ለውጥም ማሳየቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ “ምንም እንኳን እነዚህ አዎንታዊ ለውጦች ዕውቅና የተሰጣቸው እና ለሁሉም የሚታዩ ቢሆኑም የ ቡድን 7 (G7) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በ መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ያወጡት መግለጫ በሁሉም ዘርፍ የክልሉን አንገብጋቢ ፍላጎቶች ለመመለስ የተወሰዱ አንዳንድ አስፈላጊ እርምጃዎችን አላካተተም” ሲልም ሚኒስቴሩ ተችቷል፡፡
ዓለም አቀፍ ሚዲያን ጨምሮ ያልተገደበ የሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽነት አሁን ላይ “ሙሉ በሙሉ የተፈቀደ” ሲሆን በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የተፈቀደው የጋራ ምርመራም በቅርቡ እንደሚጀምርም ነው የተገለጸው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል እነዚህ እርምጃዎች ቢወሰዱም ፣ የሰብዓዊና የልማት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚገኘው ድጋፍ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ስለመሆኑም ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው ያነሳው፡፡ “የክልሉ ተግዳሮቶች ሙሉ በሙሉ እና በወቅቱ እንዲፈቱ ከተፈለገ በቂ ሀብትማሰባሰብ እጅግ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል”ም ብሏል፡፡
ከዓለም አቀፍ አጋሮች የሚቀርበው አቅርቦት ከሚያስፈልገው አንድ ሶስተኛ በታች መሆኑን ያነሳው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግስት ከ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ድጋፍ ለማድረስ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውሷል፡፡
ስለሆነም የኢፌዴሪ መንግስት የቡድን 7 ሀገራት ስጋታቸውን መግለጻቸውን የሚያደንቅ ቢሆንም ፣ የምግብ እና የመድኃኒት ዕርዳታ አቅርቦት ዋነኛ ስጋት ሆነው መቅረብ እንዳለባቸው ሚኒስቴሩ አንስቷል፡፡
የቡድን 7 ሀገራት “አመጽ እንዲቆም እና ትግራይን ጨምሮ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተቀባይነት ያለው ፣ ወደ ተአማኒ ምርጫ እና ወደ ሰፊ ብሔራዊ እርቅ የሚወስድ ግልፅ ፣ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት እንዲፈጠር” ስላቀረቡት ጥሪ ሚኒስቴሩ ያለው ነገር የለም፡፡