ስለባህር በር የሚደረጉ ንግግሮች ግራ አጋቢ እንደሆኑበት የኤርትራ መንግስት ገለጸ
መግለጫው በውሃ እና ተያያዥ ጉዳዮች ንግግሮች መብዛታቸው ከመግለጽ ውጭ በስም የጠቀሰው አካል የለም
መግለጫው የኤርትራ መንግስት እንደተለመደው በእንደዚህ አይነት መንገዶች እንደማይጠለፍ እና የሚመለከታቸው ሁሉ ጉዳዩን እንዳይነኩት አሳስቧል
የኤርትራ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ በቅርብ ጊዜ "ስለውሃ፣ ስለባህር በር እና ተዛማጅ ጉዳዮች" እየተሰሙ ያሉ ንግግሮች የሚመለከታቸውን ታዛቢዎች ሁሉ ግራ ማጋባታቸውን ገልጿል።
የኤርትራ መንግስት ይህን መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቀይ ባህር የህልውና ጉዳይ መሆኑን እና ቀይ ባህርን ለመጠቀም ንግግር እንደሚያስፈልግ ከገለጹ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።
ነገርግን መግለጫው በውሃ፣በባህር በር እና ተያያዥ ጉዳዮች ንግግሮች መብዛታቸውን ከመግለጽ ውጭ በስም የጠቀሰው አካል የለም።
የኤርትራ መንግስት እንደተለመደው በእንደዚህ አይነት መንገዶች እንደማይጠለፍ እና የሚመለከታቸው ሁሉ ጉዳዩን እንዳይነኩት አሳስቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከትናንት በስትያ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን በተላለፈ ፕሮግለራም ላይ የቀይ ባህር ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ግልጽ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ታሪክን እና የህዝብ አሰፋፈርን በመጠቀስ የኢትዮጵያን የቀይ ባህር ባለቤትነት አስረድተዋል።
ኤርትራ፣ ግብጽ እና ሱዳን ከኢትዮጵያ የሚመነጩ ወንዞችን እየተጠቀሙ ቀይባህርን አትጋሩን ማለታቸው ትክክል እንደማይሆን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀይ ባህርን የመጠቀም ጥያቄን ምክንያታዊነት ሲያስረዱ "ይሄ ውሃ ይመለከተኛል። ይሄኛው አይመለከትህም" ማለት ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ውስጥ የወደብ ጉዳይ ቸል መባሉ እና አጀንዳ አለመሆኑም ትክክል እንዳልሆነ አብራርተዋል።
"ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያሳዝነኝ እና የሚያመኝ ነገር የቀይ ባህርን ጉዳይ በፖርላማ እንኳን አንስቶ መወያየት እንደ ነውር እናስባለን።"
"አንዳንዶች አሁን ለምን ዝም አንልም፤ ጊዜው አይደለም።ከኤርትራ ጋር ያጋጨናል። ከጅቡቲ ጋር ያጋጨናል።" የሚሉ መኖራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ አተያይ አያስኬድም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በ2030፣ 150 ሚሊዮን ይደርሳል፤ 150 ሚሊዮን ህዝብን ደግሞ "የጂኦግራፊ እስረኛ(ወደብ አልባ) ሆኖ መኖር አይችልም" ብለዋል።
የወደብ ጥያቄ ህጋዊ መሆኑን እና በዚህ ጉዳይ የተደረጉ ታሪካዊ ስምምነቶችንም መለስ ብሎ መመርመር እንደሚገባም ተናግረዋል።
የወደብ ጉዳይ በጊዜ ካልተፈታ ቆይቶ ሊፈነዳ የሚችል የደህንነት ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "በአባይ ጉዳይ ለመነጋገር ማንም ፈርቶን እንደማያውቀው ሀሉ"፣ በቀይ ባህር ጉዳይም ንግግር ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን በጉልበት ወይም በጦርነት መጋራት እንደሌለባት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በጦርነት እንዳይሆን ሀቅን መካድ እና ሲል(መዝጋት)" መቅረት አለበት ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀይ ባህርን ትኩረት አድገው ይናገሩ እንጂ ኢትዮጵያ በሶሚሊያ እና በጁቡቲ በኩልም ቢሆን መተንፈሻ የባህር በር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኤርትራ በኩል ቀይ ባህርን ለመጋራት በርካታ አማራጮችን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ ካሏት ወደቦች በአንዱ ኢንቨስት እንድታደርግ፣ ኤርትራ ደግሞ ከህዳሴው ግድብ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ወይም ከኢትዮ ቴሌኮም ከ20-30 በመቶ ድርሻ ቢኖራት የሚል ሀሳብ አቅርበዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ከኤርትራ ጋር ስለመነጋገራቸው ወይም ንግግር ስለመጀመራቸው ግልጽ አላደረጉም።
በምስራቃ አፍሪካ ቀጣና ካሉት ሀገራት ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ ወደብ ካጣች ከሶስት አስርት አመታት በላይ ሆኗታል።