ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለመጠቀም እንደምትደራደር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ
ታሪክን እና የህዝብ አሰፋፈርን በመጠቀስ የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ባለቤትነት ተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቀይ ባህርን በጋራ መጠቀም አለብን ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሎች ስለህዳሴ ግድብ እያወሩ "ቀይባህርን ያህል ነገር" አትነጋገሩበት ማለት አይችሉም ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመንግስት የመገናኛ ብዙኃን በተላለፈ ፕሮግራም ላይ ቀይ ባህርን ለመጠቀም ድርድር እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ታሪክን እና የህዝብ አሰፋፈርን በመጠቀስ የኢትዮጵያን የቀይ ባህር ባለቤትነት ተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀይ ባህርን በጋራ መጠቀም አለብን ብለዋል።
- መንግስት፤ የህወሃት እና የኤርትራ ግጭት ወደ ኢትዮ- ኤርትራ ግጭት እንደማያመራ ገለጸ
- የጅቡቲና ግብጽ መሪዎች በሕዳሴ ግድብና በቀይ ባህር ላይ ያተኮረ ውይይት አደረጉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኤርትራ ተከዜን፣ ሱዳን እና ግብጽ ከኢትዮጵያ የሚመነጨውን አባይን እየተጋሩ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን እንዳትጠቀም መከልከል አይችሉም ሲሉም ተደምጠዋል።
"ይሄ ውሃ ይመለከተኛል። ይሄኛው አይመለከትህም ብትል አይሰራም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር የድርሻዋን ማግኘት እንዳለባት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የወደብ ጉዳይ ቸል መባሉ እና አጀንዳ አለመሆኑም ትክክል እንዳልሆነ አብራርተዋል።
"ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያሳዝነኝ እና የሚያመኝ ነገር የቀይ ባህርን ጉዳይ በፖርላማ እንኳን አንስቶ መወያየት እንደ ነውር እናስባለን።"
"አንዳንዶች አሁን ለምን ዝም አንልም፤ ጊዜው አይደለም።ከኤርትራ ጋር ያጋጨናል። ከጅቡቲ ጋር ያጋጨናል።" የሚሉ መኖራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ አተያይ አያስኬድም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በ2030፣ 150 ሚሊዮን ይደርሳል፤ 150 ሚሊዮን ህዝብን ደግሞ "የጂኦግራፊ እስረኛ(ወደብ አልባ) ሆኖ መኖር አይችልም" ብለዋል።
ቀይ ባህር እና የአባይ ወንዝ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሎች ስለህዳሴ ግድብ እያወሩ "ቀይባህርን ያህል ነገር" አትነጋገሩበት ማለት አይችሉም ብለዋል።
የወደብ ጥያቄ ህጋዊ መሆኑን እና በዚህ ጉዳይ የተደረጉ ታሪካዊ ስምምነቶችንም መለስ ብሎ መመርመር እንደሚገባም ተናግረዋል።
የወደብ ጉዳይ በጊዜ ካልተፈታ ቆይቶ ሊፈነዳ የሚችል የደህንነት ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "በአባይ ጉዳይ ለመነጋገር ማንም ፈርቶን እንደማያውቀው ሀሉ"፣ በቀይ ባህር ጉዳይም ንግግር ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን በጉልበት ወይም በጦርነት መጋራት እንደሌለባት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በጦርነት እንዳይሆን ሀቅን መካድ እና ሲል(መዝጋት)" መቅረት አለበት ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀይ ባህርን ትኩረት አድገው ይናገሩ እንጂ ኢትዮጵያ በሶሚሊያ እና በጁቡቲ በኩልም ቢሆን መተንፈሻ የባህር በር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኤርትራ በኩል ቀይ ባህርን ለመጋራት በርካታ አማራጮችን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ ካሏት ወደቦች በአንዱ ኢንቨስት እንድታደርግ፣ ኤርትራ ደግሞ ከህዳሴው ግድብ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ወይም ከኢትዮ ቴሌኮም ከ20-30 በመቶ ድርሻ ቢኖራት የሚል ሀሳብ አቅርበዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ከኤርትራ ጋር ስለመነጋገራቸው ወይም ንግግር ስለመጀመራቸው ግልጽ አላደረጉም።
በቀይ ባህር ዙሪያ ካሉ ሀገራት ጋር "በህዳሴ ጉዳይ፣ በተከዜ ጉዳይ እየተወያየን በቀይ ባህር ጉዳይ አንጋገርም" ማለት የሚያስከትለው አደጋ እንደሚኖር ተናግረዋል።