
የህግደፍ ዋና ጸኃፊው አል- አሚን ሙሐመድ ሰዒድ ከፓርቲው መስራቾች መካከል አንዱ ናቸው ተብሏል
የኤርትራ ገዥ ፓርቲ፤ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ፍትሕ (ህግደፍ) ዋና ጸሐፊ በ74 አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስትሩ አቶ የማነ ገብረ መስቀል በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው እንደገለጹት ከህግደፍ መስራቾች መካከል አንዱ የነበሩትና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዋና ጸሐፊ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አል- አሚን ሙሐመድ ሰዒድ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ባለስልጣኑ ለስራ በሄዱባት ሳዑዲ ዐረቢያ በድንገት ማረፋቸውን ነው የኤርትራ መንግሥት የገለጸው፡፡
አቶ አል- አሚን ሙሐመድ ሰዒድ በግንባሩ የተለያዩ ኃላፊነቶች የነበሯቸው ሲሆን በአውሮፓውያኑ ከ1977 እስከ 1987 የግንባሩ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ አል- አሚን ሙሐመድ ሰዒድ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ከአውሮፓውያኑ 1994 እስከ 2021 ድረስ ነበር፡፡
አል- አሚን ሙሐመድ ሰዒድ ከግንባሩ መስራቾ አንዱ ሲሆኑ ትግሉን የተቀላቀሉት በአውሮፓውያኑ 1966 ነበር፡፡