የአሜሪካ ማዕቀብ የተሳሳተ ፖሊሲዋ ውጤት መሆኑን ኤርትራ ገለጸች
አፍሪካ ሁሌም በግጭት ውስጥ እንድትኖር የአሜሪካ ፍላጎት መሆኑንም ኤርትራ አስታውቃለች
አሜሪካ የኤርትራ ጦርን ጨምሮ በ4 ተቋማትና በ2 ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ጥሏል
የአሜሪካ ማዕቀብ የተሳሳተ ፖሊሲዋ ውጤት መሆኑን ኤርትራ ገለጸች።
የአሜሪካው ግምጃ ቤት የኤርትራ ጦር እና የኤርትራው ገዢ ፓርቲ ህግደፍን ጨምሮ በ4 ተቋማት እና በ2 ከፍተኛ ባለስለጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።
ኤርትራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል በትናንትናው ዕለት በአሜሪካ በተጣለባት አዲስ ማዕቀብ ዙሪያ መግለጫ አውጥታለች።
ሀገሪቱ በመግለጫዋ እንዳለችው የተጣለባት አዲስ ማዕቀብ አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ እና በኤርትራ ላይ የምትከተለው የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውጤት መሆኑን ገልጻለች።
አሜሪካ ማዕቀብ ስትጥል ይህ አዲስ አይደለም ያለቸው ኤርትራ፤ ማዕቀቡ ከዓለም አቀፍ ህግ እና ከሉዓላዊነት አንጻር ትክክል ያልሆነ እና ህገወጥ ነው ብላለች።
በተጨማሪም ማዕቀቡ አሜሪካ እንዳለችው በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን ከማምጣት ይልቅ አፍሪካ በተለይም ምስራቅ አፍሪካ ሁሌም ወደ አለመረጋጋት እንዳይመጣ ያደርጋልም ብላለች ኤርትራ።
አሜሪካ ይሄንን ህገወጥ ማዕቀብ በኤርትራ ላይ ለመጣል ስትልም በማይታመኑት ብዙሃን መገናኛ ጣቢያዎች የተሳሳቱ ዘገባዎችን እና ተከፋይ የአይን ምስክሮችን መጠቀሟንም ኤርትራ በመግለጫዋ ጠቅሳለች።
የአሜሪካ ማዕቀብ ዋና አላማም ኤርትራዊያንን ለማስራብ እና በአካባቢው የፖለቲካ አለመረጋጋት በመፍጠር የራሷን ጥቅም ለማግኘት ስትል የተደረገ እንደሆነም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሰትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ የተቃወመ ሲሆን፤ “አሜሪካ እውነታውን መረዳት አልቻለችም” ብሏል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት የኤርትራ ጦርን ጨምሮ በ4 ተቋማት እና በ2 ባለስልጣናት ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
ማዕቀቡ የተጣለባቸው ሁለቱ ግለሰቦችም፤ የኤርትራ ብሄራዊ ደህንነነት ቢሮ ኃላፊ አብርሃ ካሳ ነማርያም እና የኤርትራ ህዝብ ዲሞክራሲ እና ፍትህ ንቅናቄ የኢኮኖሚ አማካሪ የሆኑት ሀጎስ ገብረህይወት ናቸው።
የኤርትራ መካላከያ ሰራዊት እና የኤርትራው ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ፍትሕ (ህግደፍ) ማዕቀብ እንተጣለባቸው የአሜሪካ ግምጃ ቤት አስታውቋል
የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ነብረት የሆነው ህድሪ ትረስት እና የቀይ ባሕር ንግድ ኮርፖሬሽንም ማዕቀቡ የተጣለባቸው ተቋማት መሆናቸውም ታውቋል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ማዕቀቡ የተጣለባቸው ተቀዋማት እና ግለሰቦች በአሜሪካ ያላቸው ንብረት እንዳይንቀሳቀስ እና የጉዞ እገዳን ያካትታል።