ኢትዮጵያ፤ አሜሪካ በኤርትራ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ተቃወመች
የአሜሪካ ግምጃ ቤት የኤርትራ ጦርን ጨምሮ በ4 ተቋማትና በ2 ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ጥሏል
የአሜሪካና የአለም ማህበረሰብ ትክክለኛ የማዕቀብ ኢላማ ህወሓት ላይ ሊሆን እንደሚገባም መንግስት ጠይቋል
ኢትዮጵያ የአሜሪካው ግምጃ ቤት በትናትናው እለት በኤርትራ ለይ የጣለውን ማዕቀብ ተቃወመች።
የአሜሪካው ግምጃ ቤት የኤርትራ ጦር እና የኤርትራው ገዢ ፓርቲ ህግደፍን ጨምሮ በ4 ተቋማት እና በ2 ከፍተኛ ባለስለጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሰሳል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ የተቃወመ ሲሆን፤ “አሜሪካ እውነታውን መረዳት አልቻለችም” ብሏል።
“ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ሉአላዊ ሀገር ወደ ሆነችው ኤርትራ ሮኬቶችን ተኩሷል” ያለው ሚኒስቴሩ፤ “በግዛታዊ አንድነቱ እና ደህንነቱ ላይ የተደቀነውን አደጋ መከላከል የኤርትራ መንግስት መብት ነው” ሲል አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ባሳለፍነው ዓመት ሰኔ ላይ የተናጥል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ የኤርትራ መንግሰትም ጦሩን ከኢትዮጵያ ማስወጣቱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውሷል።
“የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን እንቅፋት ነው ብሎ አያምንም” ያለው ሚኒስቴሩ፤ “በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አሁን ያለው እውነተኛና የሰላም ስጋት የህወሓት ቀጣይነት ያለው ጠብ አጫሪነት እና የወረራ ተግባር ነው” ብሏል።
“የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የህወሓትን የጠብ አጫሪነት ተግባራት አጥብቆ ለማውገዝ አለመፈለጉ የሽብር ቡድኑን አበረታቶታል” ሲልም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።
የማዕቀብ ዋነኛ አላማ ጠብ አጫሪ አካላት ተግባራቸውን እንዲያቆሙ ለማስገደድ ከሆነ፣ የአሜሪካ መንግስት እና የአለም ማህበረሰብ ትክክለኛ የማዕቀብ ኢላማ ህወሓት ላይ ሊሆን እንደሚገባም መግለጫው አመላክቷል።
ስለሆነም የአሜሪካ መንግስት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንደገና እንዲያጤንና እንዲሰርዝ የጠየቀው መግለጫው፤ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፈተናዎች ዋነኛ መንስኤ የሆነው ህወሓት ላይ እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቋል።
የአሜሪካው ግምጃ ቤት በትናትናው እለት በአራት የኤርትራ ተቋማት እና በሁለት የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።
ማዕቀቡ የተጣለባቸው ሁለቱ ግለሰቦችም፤ የኤርትራ ብሄራዊ ደህንነነት ቢሮ ኃላፊ አብርሃ ካሳ ነማርያም እና የኤርትራ ህዝብ ዲሞክራሲ እና ፍትህ ንቅናቄ የኢኮኖሚ አማካሪ የሆኑት ሀጎስ ገብረህይወት ናቸው።
የኤርትራ መካላከያ ሰራዊት እና የኤርትራው ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ፍትሕ (ህግደፍ) ማዕቀብ እንተጣለባቸው የአሜሪካ ግምጃ ቤት አስታውቋል
የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ነብረት የሆነው ህድሪ ትረስት እና የቀይ ባሕር ንግድ ኮርፖሬሽንም ማዕቀቡ የተጣለባቸው ተቋማት መሆናቸውም ታውቋል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ማዕቀቡ የተጣለባቸው ተቀዋማት እና ግለሰቦች በአሜሪካ ያላቸው ንብረት እንዳይንቀሳቀስ እና የጉዞ እገዳን ያካትታል።