አቶ ኢሳያስ ጅራ የሴካፋ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በድጋሚ ተመረጡ
የታንዛንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዋላስ ካይራ ሴካፋን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠዋል
አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ በቅርቡ በድጋሚ መመረጣቸው ይታወሳል
የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበር (ሴካፋ )የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ በዛንዚባር ሆቴል ቨርድ የአባል ሀገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል።
ጉባኤው ለሚቀጥሉት አራት አመታት ሴካፋን በፕሬዝዳንትነት እና በምክትል ፐሬዝዳንትነት የሚመሩት አመራሮች መምረጡም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
በዚህም ጉባኤው ቀደም ሲል ሴካፋን ሲመሩት የነበሩትን የታንዛንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዋላስ ካይራ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራን ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ሴካፋን በፕሬዝዳንትነት እና ምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ በድጋሚ መርጠዋል፡፡
አቶ ኢሳያስ ጅራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ባሳለፍነው ወርሃ ነሃሴ በተደረገው በ14ኛው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ በድጋሚ መመረጣቸው የሚታወስ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከተመረጡ በኋላ የኢትዮጵያን እግር ኳስን ወደ ተሻ ደረጃ ለማድረስ ቃል መግባታቸውም አይዘነጋም፡፡
አቶ ኢሳያስ "ብሔራዊ ሊግን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የሊግ ውድድሮች የቴሌቪዥን ስርጭት እንዲያገኙ" እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር፡፡
በተጨማሪም የፌዴሬሽኑን ተቋማዊ አደረጃጀት ከማጠናከር በዘለለ፣ ከሊግ ካምፓኒው ጋር በመተባበር "ክለብ ላይሰንሲንግ" ላይ ለመስራት፣ ተጨማሪ የልምምድ ስፍራዎችን ለመገንባት፣ የአሰልጣኞችን አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ ስልጠናዎችን ለመስጠት እንዳቀዱ ተናግረዋል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ላይ ከመስራት እና ለክልል ፌዴሬሽኖች የተሻለ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የሙያ ማህበራትን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ለዚህ የሚሆንና ለቀጣዮቹ 4 ዓመታት የሚያገለግል "ሌጋሲ ዶክመንት" አዘጋጅተናል ያሉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፤ የተጫዋቾች ዝውውር መነሻውን ከ2 ዓመት ከፍ በማድረግና ጣራውን እስከ 5 ዓመት በማድረግ የተረጋጋ የኮንትራት ይዞታን ለመፍጠር እንደሚሰሩም ቃል ገብቷል፡፡