ኢኤስፒኤን ቀነኒሳ እና ጥሩነሽን ጨምሮ ምርጥ ያላቸውን የአፍሪካ ስፖርተኞች ይፋ አደረገ
ኢኤስፒኤን አህጉሪቱ ካላት ስፋት እና የስፖርት ብዛት አንጻር 25 "ምርጥ" መለየት ፈታኝ ነው ብሏል
ኢኤስፒኤን ቀነኒሳ በቀለን እና ጥሩነሽ ዲባባን ጨምሮ በ21ኛው ክፍለዘመን ምርጥ ያላቸውን የአፍሪካ ስፓርተኞች ይፋ አድርጓል
የአሜሪካው አለምአቀፍ የስፓርት ቻናል(ኢኤስፒኤን) ቀነኒሳ በቀለን እና ጥሩነሽ ዲባባን ጨምሮ በ21ኛው ክፍለዘመን ምርጥ ያላቸውን የአፍሪካ ስፓርተኞች ይፋ አድርጓል።
ኢኤስፒኤን አህጉሪቱ ካላት ስፋት እና የስፖርት ብዛት አንጻር 25 "ምርጥ" መለየት ፈታኝ ነው ብሏል።
ዓለም ካየቻቸው ምርጥ የማራቶን ሯጭ አንዱ ከሆነው ኢሉድ ኪፕቾጌ እና ኦሎምፒክ እና በርካታ የአውሮፓ ሻሜፒዮን ሽፕ አሸናፊ ከሆነው ሳሙኤል ኢቶ ማንን ትመርጣላችሁ? ሲል ይጠይቃል።
ያም ሆነ ይህ ደረጃውን አውጥተነዋል" ያለው ኢኤስፒኤን ጉዳዩን" ወደማህበራዊ ሚዲያ ወስዳችሁ ብትወያዩበት ምን ያህል እንደተሳሳትን ቢነግሩት ቅር እንደማይለው ጠቅሷል።
ነገርግን እንድታስታውሱ የምንፈልገው፣ እያወራን ያለነው ከፈረንጆቹ 2000 ወዲህ ስፓርታዊ ውድድሮችን ስለጀመሩ እና አፈጻጸማቸው ከፍተኛ ደረጃ ስለደረሱ አትሌቶች ነው ሲል ኢኤስፒኤን በአጽንኦት ተናግሯል።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በቻናሉ ዘገባ የ21ኛው ክፍለዘመን ምርጥ የአፍሪካ ስፖርተኛ ተብሎ ስሙ በመካተቱ እንደተደሰተ በፌስ ቡክ ገጹ ጽፏል።
አትሌት ቀነኒሳ በ2000ዎቹ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ሩጫዎች የበላይነት በመያዝ እስከ 2020 ድረስ የሁለቱም ርቀቶች ሪከርዶች በእሱ እጅ ነበሩ። ቀነኒሳ በቀለ 3 ወርቅ በኦሎምፒክ ፣ 5 ወርቅ በአለም ሻምፒዮን ሽፕ፣ 11 ወርቅ በሀገር አቋሯጭ መሰብሰባ የቻለ አትሌት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ቀነኒሳ በቀለ ሁለት ጊዜ የበርሊን ማራቶንን ማሸነፋ ችሏል።
ሌላዋ የሀገሩ ልጅ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባም በዚህ ቻናል ምርጥ ከተባሉት አትሌቶች አንዷ ነች።
አትሌት ጥሩነሽም ሶስት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጨሞሮ በበርካታ አለምአቀፍ ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
በዘገባው ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ፣ ካሜሩናዊው ሳሙኤል ኢቶ፣ የዚምባብዌዋ ዋናተኛ ክርስቲ ኮቨንትሪን እና በርካታ የፕሪሜር ሊግ እና የአውሮፓ ሻምፒዮን ሽፕ ጨዋታዎችን ያሸነፈውን ድዲየር ድሮግባን ጨምሮ 25 ስፖርተኞች ምርጥ ተብለዋል።