ቀነኒሳ ከውድድሩ ውጭ የሆነው በግራ እግሩ ላይ በገጠመው ምክንያት ነው
ቀነኒሳ በቀለ ከሎንደን ማራቶን ውጪ ሆነ
በማራቶን ታሪክ እጅግ ፈጣኑ ሁለተኛው ሰው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የፊታችን እሁድ እንደሚካሄድ ከሚጠበቀው የሎንደን ማራቶን ውጭ መሆኑ ተነገረ፡፡
ከኬንያዊው የውድድሩ የሪከርድ ባለቤት ኤሉድ ኪፕቾጌ ጋር ጥብቅ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቅ የነበረው ቀነኒሳ በባቱ ላይ በገጠመው ጉዳት ምክንያት ከውድድሩ ውጭ ለመሆን መገደዱን ገልጿል፡፡
ቀነኒሳ ወረርሽኙ ሁሉን ይፈትን በነበረበት ሰዓት ጭምር ከስልጠና አባላቱ ውጪ ፈታኝ ልምምዶችን ሳደርግ ነበር ነው ያለው፡፡
ሆኖም በሁለት የፍጥነት ልምምድ ክፍለ ጊዜዎች በግራ ባቱ ላይ ህመም አጋጥሞታል፡፡
ከዛን ጊዜ ጀምሮ በየቀኑ ህክምናዎችን ቢያደርግምና ለወድድሩ ሊደርስ እንደሚችል ቢያስብም ህመሙ እየተባባሰ መምጣቱንና በውድድሩ ሊሳተፍ እንደማይችል ማወቁን ገልጿል፡፡
ለእኔ ጠቃሚ ነው ባለው ውድድር መሳተፍ አለመቻሉ እጅግ እንዳሳዘነውም ነው የተናገረው፡፡
ቀነኒሳ ባለፈው ዓመት የበርሊን ማራቶንን 2፡01 በመግባት አሸንፎ ነበር፡፡
ይህ በውድድሩ አሸናፊ ሆኖ ለመቅረብ የሚያስችል ስነ ልቦናን አላብሶኝ ነበርም ብሏል፡፡
አድናቂዎቹንና የውድድሩን አዘጋጆች ይቅርታ የጠየቀም ሲሆን ምናልባትም በቀጣዩ ዓመት ከህመሙ አገግሞ ወደ ሎንደን ሊመለስ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
የወድድሩ የባለፈው ዓመት 2ኛ እና 3ኛዎች ሞስነት ገረመው እና ሙሌ ዋሲሁን የውድድሩ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡