ኢኮኖሚ
በፀጥታ ስጋት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀመረ
የባቡር ትራንስፖርቱ ባሳለፍነው ሳምንት በአፋርና ሶማል ክልል አዋሳኝ ስፍራዎች በተፈጠረ ግጭት ነበር አገልግሎቱን ያቆመው
የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራት ዓመት ሊሞላው ነው
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር ከሀምሌ 19 ቀን 2013 ዓ.ም አንስቶ በአፋር እና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረ የጸጥታ ስጋት ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቁሞ ነበር።
በተቋሙ የባቡር ደህንነት ሃላፊው ኢንጅነር ጥበቡ ተረፈ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት በጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ጀምሯል።
የመንገደኞች እና የእቃ ማጓጓዝ ትራንስፖርት አገልግሎቱ ካሳለፍነው ቅዳሜ ሀምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም አንስቶ አገልግሎቱ መሰጠት መጀመሩን ኢንጅነር ጥበቡ ገልጸዋል።
አገልግሎቱ የተጀመረው ከፌደራል፤ ከክልሎቹ አመራሮች እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ እንደሆነም ተገልጿል።
752 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ከፈረንጆቹ ጥር 2018 ጀምሮ የመንገደኞች እና የእቃ ማጓጓዝ ትራንስፖርት በመስጠት ላይ ይገኛል።
የባቡር መስመር ፕሮጀክቱ 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፤ 70 በመቶው ከቻይና መንግስት በተገኘ ብድር 30 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ መገንባቱ ይትወሳል።